Tuesday, September 6, 2011 11:02:00 PM
ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡ ዕብ. 13.1-2 ፡፡[/SIZE]በየዓመቱ ጳጉሜ 3 የቅዱስ ሩፋኤል መልአክ መታሰቢያ ነው ፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡
የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላ ‹አባባ የነገርከኝን ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እፈጽማለሁ ግን ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? ሀገሩን አላውቀውም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሩ አሳሳቢ ሆኖ ስላገኘው ጦቢት ልጁ ጦብያን ‹አብሮህ የሚሄድ ሰው እስቲ ፈልግ ምናልባት አብሮ የሚሄድ ጓደኛ ታገኝ ይሆናል ደመወዝም ሰጥተን ቢሆን ካንተ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ ያስፈልግሃልና ሂድ ሰው ፈልግ› አለው፡፡
አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ቢሄድ አንድ መልካም ጐበዝ አገኘ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ጦብያ ግን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጦብያ መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘው ‹የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን የድካምህን ዋጋ የጠየቅኸውን ያህል እሰጥሃለሁ› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ‹እሺ ካንተ ጋር ለመሄድ ፈቃኛ ነኝ መንገዱንም ሆነ ሀገሩን በሚገባ አውቀዋለሁ ከገባኤል ቤት ብዙ ጊዜ ኑሬአለሁና› አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ጦብያ በል ከአባቴ ጋር ላስተዋውቅህ ብሎ ወደ አባቱ ወስዶ አስተዋወቀው ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው በማለት ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም የታላቅ ወንድምህ ወገን ከመሆንም ሌላ ስሜም አዛርያስ ይባላል አለው፡፡
ጦቢ. 5.12 ፡፡ ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ‹አንተስ ወንድሜ ነህ በል የልጄ የጦብያን ነገር አደራ ከሀገር ወጥቶ አያውቅምና እንዳይደነግጥ ደኅና አድርገህ እንድትይዝልኝ› ብሎ ስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል ‹መራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡ እነርሱ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው ፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው ፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው ፡፡ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡
ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፣ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው አደረጉት፡፡ ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን እንደሚያገለግል ለመረዳት ‹ይህን ያዘው ያልከኝ ለምንድን ነው?› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ጋኔን ያደረበት ሰው ሲገኝ ይህንን ከዕጣን ጋር ቢያጤሱበት ጋኔኑ ይለቃል ሲል መለሰለት፣፡
በዚህ ሁኔታ አንድ ባንድ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ‹ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱ ዘመድህ ነው፡፡ የእርሱም ልጅ ሣራ የምትባል ቆንጆ ልጅ አለችው፡፡ እሷን ለሚስትነት ይሰጥህ ዘንድ ለራጉኤል እነግርልሃለሁ› አለው፡፡
ጦብያም ‹ያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ እንደሚያድሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን መሰለህ ያዘው ያልኩህ ? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳለው ሚስቱ አድናን ‹ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል› አላት ከዚያም ጋር አያይዞ ‹ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነሱም ‹ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን› አሉት፡፡ ‹ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት ‹እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ› አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል ‹የወንድሜ ልጅ ነህን?› ብለ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
ራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ ‹መልአከ ከብካብ› ይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የ14 ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡
ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ
የ14 ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡
በመጨረሻም ከጦብያ ጋር ሄዶ የነበረው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት ጠሩት እርሱ ግን ጦቢትንና ጦብያን ‹ፈጣሪያችሁን አመስግኑ እናንተ እስከ ዛሬ ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ /መጽ. ጦቢት/፡፡
ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡ ዕብ. 13.1-2 ፡፡
ጦቢት ከእህሉ ከፍሎ ለተራበ የሚያበላ ከልብሱ ለተራቆተ ሰው የሚያለብስ እግዚአብሔርን ዘወትር የሚያመሰግን ለወገኖቹ የሚራራ አሥራት በኩራት የሚያወጣ ሰው ነበር፡፡ በመሆኑም በሥራው ሁሉ እንዲረዳው በችግሩ ጊዜ እንዲያጸናው ቅዱስ ሩፋኤል ተልኮለታል፡፡ እኛም በሕይወታችን የጐደለብንን ነገር እንዲሞላልን ጐዳናችንን እንዲያስተካክልልን ከክፉ ጋኔን እንዲጠብቀን አምላክ ቅዱስ ሩፋኤል ተለመነን ቅዱስ ሩፋኤልንም አማልደን ማለትን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ጳጉሜ የዘመን መሸጋገሪያ እንደ ሆነች ዕለተ ምጽአትም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንሸጋገርባት ስለሆነች ከወዲሁ የቅዱስ ሩፋኤልን የመታሰቢያ በዓሉን ስናከብር በአማላጅነቱ ከቅዱሳን ኅብረት እንዲደምረን በንስሐ ታጥበን ደጅ ልንጠና ይገባል፡፡[/B]
የቅዱስ ሩፋኤል ልመናው ይደረግልን በረከቱ ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
Thursday, October 7, 2010 9:04:43 AM
በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን እስከ ኅዳር 6 ቀን ያለው ጊዜ ወርኀ ጽጌ ይባላል፡፡ ይህ ወቅት ምድር በአበቦች ቀለምና መዓዛ የምታጌጥበት በመሆኑ «የአበባ ወር» ወርኀ ጽጌ ተብሏል፡፡
አበባ የፍሬ እናት ነው፡፡ አበባን ያየ ሰው ሕይወቱ በተስፋ ትሞላለች፡፡ መልካሙ ፍሬ ከአበባው ይገኛልና፡፡ እመቤታችንም የተባረከ ፍሬ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርሰቶስን ያስገኘች አማናዊቷ አበባ ናት፡፡ የአዳም ተስፋ መፈጸሙን፣ የነቢያት ትንቢት መድረሱን ያበሰረችን የድኅነት ምልክት እርሷ ናት፡፡ «ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል» እንዳለ ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ (ኢሳ 7÷14)፡፡
የአበቦች መፍካት የጥጋብ ዘመን መምጣጡን ያበስራል፡፡ ወርኃ ክረምት ዘር ገና በምድር ላይ ስለሆነ ጎተራው ይሟጠጣል፡፡ መሶቡ ድንግጥ ይላል፡፡ የክረምቱ ጊዜ በጎመንና በቅጠላ ቅጠሉ በጥራጥሬው ጭምር ይወጣል፡፡ ከአዲሱ ዘመን መባቻ ጀምሮ ግን «የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ» በሚለው ባሕላዊ አገላለጽ የአዲስ እህል ሽታ ይሰማል፡፡ የእሸት ጊዜ ይታያል፡፡ ይህ ጊዜ ምድር በሥነ ጽጌያት ( በአበቦች ኅብር) አጊጣ፣ ሰማይ በከዋክብት አሽብርቆ የሚታይበት፣ የጠራ ውኃ ከወንዞችና ጅረቶች የሚፈስበት፣ ንፁሕ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ ከተሰደዱበት እየተመለሱ የሚዘምሩበት፣ እንስሳትና አራዊት ለምለሙን ሳር እየነጩ ጥሩውን ወሃ እየተጎነጩ የሚፈነድቁበት ጊዜ ስለሆነ ለፍጥረት ደስ ይላል (መኃልይ 2÷13)፡፡
«የዘንድሮን ክረምት ወጣናት በመላ
አንድ ቀን ሰናድር አንድ ቀን ስንበላ
እኛስ ይችን ክረምት ወጣናት በመላ
በኩርማን እንጀራ ጎመን ተጠቅልላ»
እንደሚባለው ክረምት ያለችውን አብቃቅቶ የሚከረምበት ጊዜ ነው፡፡ አበቦች በጋራ በሽንተሩ ሲፈነዱ ማሳውና ጓሮው ሲያብብ ግን የጥጋቡ የእህሉ ወቅት መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
የድኅነት ምግብ የጽድቅ ውኃ አጥቶ በሲዖል በረሃ በጽድቅ ረሃብ ለተንገላታው የአዳም ዘር ነፍስ በእግዚአብሔር ቸርነት በጌታችን ሥጋና ደም በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የምትጠግብበት ዘመን መድረሱን ያበሠረችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ዛሬም ቢሆን የተስፋ መቁረጥና የጭንቀት፣ የደዌ ሥጋና የደዌ ነፍስ ረሃብ ለወደቀባቸው እመቤታችን የመዳን ተስፋቸው ናት፡፡ በዚህም የተነሳ ቅዱሳን አበው እመቤታችንን በአበባ መስለው ምስጢር ከምሳሌ በማስተባበር ስደቷን በወርኃ ጽጌ ያስቡታል፡
ይህ የእመቤታችን መታሰቢያ ወር በቤተክርስቲያናችን የሚከበረው በሚከተለው ሁኔታ ነው፡፡
1ኛ. በማኅሌት
2ኛ. በቅዳሴ
3ኛ. በዝክር
ማኅሌት
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፣ በአምላካችን ቤት በአደባባዮች የምትቆሙ እናንተ የእግዚአብሔር ባርያዎች ሁላችሁ በሌሊት እጃችሁን አንሱ፣ እግዚአብሔርንም ባርኩ (መዝ 133÷1-2) በማለት እንደተናገረው አባቶቻችን ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት እንዲሁም በክብረ በዓላት እጆቻቸውን ለጭብጨባና ለሽብሸባ አንስተው፣ በከበሮና በጸናጽል እየወረቡ፣ በመቋሚያ እየዘመሙ፣ ያለ ድካምና መሰልቸት ሲዘምሩ ያድራሉ፡፡ ምዕመናንም እንቅልፍ ሳያታልላቸው፣ ድካም ሳይበግራቸው ከአባቶቻቸው ጋር በቤተክርስቲያን በመገኘት በዕልልታ በዝማሬ እያጀቡ ያድራሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሚቀርበው ዝማሬ ሦስት ወገን ነው፡፡
1. ከቅዱስ ያሬድ ድጓ
ቤተክርስቲያናችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሳወቋት ሊቃውንተ ቤተክርሰቲያን መካከል አንዱና ዋነኛው ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ከአርያም የተገኘ በመሆኑ ጊዜ የማይሽረው ዘመን የማይለውጠው የቅድስት ቤተክርስቲያን አንጡራ ሀብት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመቱን ክረምት፣ መጸው፣ ሐጋይ ፀደይ ብሎ በመከፋፈል በየዘመኑ የሚዘመረውን መዝሙር አዘጋጅቷል፡፡ በወርኃ ጽጌም ቅዱስ ያሬድ የምድሪቱን በአበባ መሸለም፣ በቡቃያ ማማር፣ የክረምቱን የጭቃና የድጥ ወቅት ማለፍ በተመለከተ እግዚአብሔርን ካመሰገነበት ድርሰቱ እየተውጣጣ ይዘመራል፡፡ በተለይ በወርኀ ጽጌ፡፡
2. ማኅሌተ ጽጌ
ይህ መዝሙር የእመቤታችንን ታሪክ ከጽንሰቷ እስከ ልደቷ፣ ክብሯን፣ ንጽህናዋን፣ በሄሮድስ ምክንያት የደረሰባትን ስደትና መከራ የበረሀውን ጉዞ እያነሳ የሚያመሰግን ታሪካዊ ይዘት ያለው ድርሰት ነው፡፡
ማኅሌተ ጽጌን የደረሱት አባ ጽጌ ብርሃን የተባሉ ሊቅ መሆናቸው ይነገረል፡፡ ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ የምሁርን ሕዝብ አስተምረው ወደ ይፋት በማምራት ወንጌልን በመስበክ ላይ እያሉ «ክርስቶስ ተወለደ፣ ሞተ፣ ተነሣ እያሉ እንዴት ያስተምራሉ;» በማለት አንድ አይሁዳዊ ሊቅ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 11 ቁጥር አንድ ላያ የጻፈውን የነቢዩን ቃል («ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከሥሩም ቄጥቋጦ ያፈራል» የሚለውን) ጠቅሰው ስላብራሩለት በትምህርታቸው አምኖ ተጠምቆ ለመመንኮስ በቅቷል፡፡ ስሙንም ጽጌ ብርሃን በማለት ሰይመውታል፡፡
አባ ጽጌ ብርሃን ምሁረ ኦሪት ስለነበረ አብሯቸው እየተዘዋወረ ሀዲስን ከብሉይ አስማምቶ ከተማረ በኋላ እንደ መዝሙረ ዳዊት 150 አድርጎ ማኅሌተ ጽጌን ከአማካሪው ከወረ ኢለኀው ተወላጅ ከአባ ገብረማርያም ዘደብረ ሐንታ ጋር በመሆን አዘጋጀው፡፡ ድርሰቱም ቤት እየመታ በአምስት በአምስት ስንኝ እየተከፈለ ነው፡፡
በዚህ ጊዜም ጾም የጌታንና የእመቤታችንን ስደትና መንገላታት በማሰብ ስለ ፍቅራቸው ባሕታውያን፣ መነኮሳትና አንዳንድ ምዕመናን በፈቃዳቸው ይጾማሉ፡፡
3. ሰቆቃወ ድንግል
«ሰቆቃ» ማለት ለቅሶ ዋይታ ማለት ነው፡፡ እመቤታች «ልጄን ይገድሉብኛል ብላ የሄሮድስ ወታደሮች ሲከተሏት፣ የዮሴፍ ልጅ ዮሳዕ የቤተልሔምን ሕጻናት እልቂት ሲነግራት፣ ጥጦስና ዳክርስ የተባሉ ከግብጽ ወደ እስራኤል በሚወስደው መንገድ በጋዛ በር የሚዘርፉ ሽፍቶች ሲያጋጥሟት ያለቀሰችውንና በተወደደ ልጇ ላይ የወረደውን መሪር እንባ በማስታወስ የሚዘመር ነው፡፡ ይህም መዝሙር በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በደብረ ወርቅ ቤተክርስቲያን የድጓ መምህር በነበሩት በመምህር አርከ ሥሉስ እንደተደረሰ ይነገራል፡፡ (ማ/ቅዱሳን ድረ ገጽ)[/SIZE][/COLOR]
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Friday, August 6, 2010 8:13:30 PM
ጾመ ፍልሰታን እንዴት እናክብር?በሕይወተ ሥጋ ሳለን ካልጾምንና ካልጸለይን ነፍሳችን ልትለመልም አትችልም፡፡ በጾም በጸሎት ዲያብሎስን፣ ዓለምንና ፍትወታት እኩያትን ድል መንሣት ይቻላል፡፡ እንደዚሁም በጾም አማካኝነት መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ይቻላል፡፡
ውድ አንባቢያን ለመግቢያ ያህል ስለጾም ይህን ያህል አልን እንጂ ጾም በራሱ ምንድን ነው? ለምንስ ይጾማል? ምንስ ጥቅም ያስገኛል? ባንጾምስ ምን ጉዳት አለው ?የሚሉትን በአጭር በአጭሩ ከገለጽን በኋላ በዋናነት ስለተነሣንበት ዐቢይ ርእስ ስለፍልሰታ ጾም በስፋት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የፍልሰታ ጾም ከሰባቱ አጽዋማት አንዷ ነች፡፡ በደመቀና በተለየ ሁኔታ የምትጾምበት ምክንያት ምን እንደሆነና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች በማንሳት የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንት መልስ ጭምር ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ፡፡
«ጾም» ማለት «ጾመ» ተወ፣ ታቀበ፣ ታረመ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን የቃሉ ትርጉም ደግሞ ምግብ መተው፣ መከልከልና መጠበቅ ማለት ነው ሲሉ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ በ1995 ዓ.ም «ጾምና ምጽዋት» በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 8 ላይ ገልጸውታል፡፡ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ ምዝገበ ቃላትም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው፡፡
ጾም ጥሉላት መባልዕትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌላውም ክፉ ነገር ሁሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቆጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብና እርሱንም ደጅ መጥናት ነው፡፡ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ደጉ ዓለም ካሣ እና ቀሲስ ስንታየሁ አባተም የሚገልጹት ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡
«መላው ሕዋሳታችን ካልጾሙ የምግብና መጠጥ ጾም ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ መጽሐፉም የሚለው «ወደ አፍ የሚገባ ሰውን አያረክስም፤ ከአፍ የሚወጣ እንጂ፡፡» ስለዚህ ዐይን፣ ጆሮ፣ እግርና እጅ የመሳሰሉት የስሜት ሕዋሳታችን መጾም አለባቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ ይልቅ የሚበልጡት እነዚህ ናቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ የምንቆጠበው በራሱ ኃጢአት ስለሆነ ሳይሆን ምግብና መጠጥ ሥጋን አጥግቦ በገደል ስለሚጥል ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ስለሚጎትት እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ በዋናነት ስንጾም ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከዝሙትና በሐሰት ከመመስከር ወዘተ መቆጠብ አለብን» ሲሉ መምህር ደጉ አመልክተዋል፡፡
የጾም መሠረቱ ሃይማኖት ነው፡፡ በሃይማኖት የተነሣ ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጾም ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለት ዓይነት መስመር አለው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአጽዋማት ወቅት ከምግበ ሥጋና ከኃጢአት ትከለክላለች፡፡ ከኃጢአት ሁልጊዜ እንከላከላለን፡፡ ከምግብ የምንከለከለው ምግብ ኃጢአት ስለሆነ ሳይሆን ከሃይማኖት የተነሣ ነው፡፡ ምግብ በልተን ፍቃደ ሥጋችንን ከምናደልብ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋችንን ጎስመን ከሞት በኋላ ከሰማይ የሚኖረን ሕይወት ያለምግብና መጠጥ በምስጋና እያመሰገንን የምንኖርበትን ሕይወት የምናስብብት ነው ያሉት ደግሞ ቀሲስ ስንታየሁ አባተ ናቸው፡፡
«ኃጢአትን ደግሞ ስንጠመቅ ለኃጢአት ሞተን፣ ለጽድቅ የተነሣን ስለሆንን ሁልጊዜ ኃጢአትን ትተን በንጽሕና፣ በቅድስና የምንኖርበት ሁኔታ ነው፡፡ ነገር ግን ከዕውቀት ጉድለት የተነሣ ሥጋዊን ምግብ ብቻ አንዳንድ ሰዎች ሊተውት ይችላሉ፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት አይደለም፡፡ ዋጋ እንዲኖረን /እንድናገኝ/ ኃጢአቱን፣ ቂም በቀሉን፣ ክፋቱን፣ ማንኛውንም በእኛ ላይ እንዲደረግብን የማንፈልገውን ነገር ሌሎች ላይ ማድረግን ትተን ምግብን ለተወሰነ ሰዓት እንጾማለን» በማለት ቀሲስ ስንታየሁ አክለው ተናግረዋል፡፡
ጾም የግልና የዐዋጅ /የሕግ/ ጾም በመባል ይከፈላል፡፡ የግል ጾም የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የዐዋጅ /የሕግ/ ጾም በሰባት የሚከፈል ሲሆን እነዚህም ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/፣ ጾመ ነቢያት /የገና ጾም/፣ ጾመ ገሃድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ረቡዕና ዓርብ እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም ከሰባቱ አንዱ በሆነችው ጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፍልሰታ ጾም ስለሆነ ነው፡፡
ፍልሰታን ከሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ ልዩ የሚያደርጋት ምን እንደሆነ እናያለን፡፡ የፍልሰታን ጾም ሕፃን አዋቂው ሳይቀር በልዩ ሥነ ሥርዓትና በደመቀ ሁኔታ ይከናወናል፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞችና በግል የሥራ መስክ የተሰማሩ ሁሉ የዕረፍት ጊዜ በመውሰድ በገዳማትና በየአብያተ ክርስቲያናት ሱባኤ በመግባት ከነሐሴ አንድ ጀምሮ እስከ አሥራ ስድስት ቀን ድረስ ጾም ጸሎት በማድረግ ይቆያሉ፡፡ ጾም ጸሎት ሲያደርጉ ደግሞ በድሎት ሳይሆን በየዋሻው፣ በየመቃብር ቤቱና አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ እንጨት ረብርበውና ሳር ጎዝጉዘው ጥሬ እየበሉ ነው፡፡
ፍልሰታ ምን ማለት ነው? በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ደጉ ዓለም መልስ አላቸው፡፡ «ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፣ ተሰደደ ከሚለው ግስ የወጣ ነው፡፡ ፈለሰ ማለት ደግሞ የተለያየ ትርጉም ቢሰጠውም ፍልሰታ ለማርያም ብሎ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ወደ ማያልፈው ዓለም ከመቃብር የወጣችበት /የተነሣችበት/ ቀን ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሥጋዊው ዓለም ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተሸጋገረችበት ነው፡፡»
በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት ክፍል ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ቀሲስ ስንታየሁ አባተ በበኩላቸው «ፍልሰታ ለማርያም የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ፍልሰታ ማለት ደግሞ ፈለሰ ከሚል ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ፈለሰ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድን /መፍለስን/ ያመለክታል፡፡ ይኸውም እመቤታችን በሐዋርያት ዘመን ካረፈች በኋላ የሥጋዋን መፍለስ አስመልክቶ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደተቀበረ አላወቁም ነበርና እግዚአብሔር ያንን እንዲገልጥላቸው ስለ እመቤታችን ዕረፍት አስመልክቶ የጾሙት ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት ሁለት ሱባኤ ጾመው የእመቤታችንን ሥጋዋን ሰጥቷቸው ትንሣኤዋን፣ ዕርገቷን ያዩበት ሁኔታ ስለነበርና በረከት ያገኙበት ጾም ነው፡፡ ስለሆነም ምእመናን ፍልሰታ ለማርያምን ከልጅ እስከ አዋቂው በጾም በጸሎትና በመቁረብ በጋራ በፍቅር፣ በሰላም ያሳልፉታል፡፡»
መምህር ደጉ ዓለም ካሣ እንዳብራሩት ከሆነ ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን እንዲጠብቃት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት የእመቤታችን ነገር እንዴት ነው?ብለው በጠየቁት ጊዜ «እመቤታችንማ በገነት በዕጸ ሕይወት ሥር ናት» ብሎ ነገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሐዋርያት እመቤታችን ከመቃብር መነሣቷንና ማረጓን ማየት አለብን፤ እንዴት ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በመንፈሳዊ ቅናት በመነሳሳት ነሐሴ አንድ ቀን በዕለተ ሰኞ ሁለት ሰባት ሱባኤ ያዙ፡፡ በ14ኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ አንሥቶ ሰጣቸውና በጌቴ ሴማኒ ቀበሯት፡፡ እመቤታችን በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን ዐርፋ ነሐሴ 14 ቀን ልትቀበር ችላለች፡፡
ይሁንና ሐዋርያት ቢቀብሯትም መነሣቷ ዕርገቷን አላዩም ነበር፡፡ መነሣቷን ዕርገት ያየው ነገር ግን ሲቀብሯት ያላየው ትውልዱ ከሰዶቃዊ የሆነ ቶማስ ነው፡፡ ቶማስ እንዲያስተምር ሕንድ ሀገር ዕጣ ደርሶት አስተምሮ በደመና ሲመለስ ነሐሴ 16 ቀን እመቤታችን ስታርግ በሕዋ ላይ ተገናኙ በማለት መ/ር ደጉ አስረድተዋል፡፡ እንደ መምህር ደጉ ገለጻ የፍልሰታ ጾም የሚጾመው ልክ ሐዋርያት ሁለት ሰባት ሱባኤ ይዘው ለ14 ቀን የሚጾም ቢሆንም አባቶቻችን ግን እመቤታችን የተነሣችበትንና ያረገችበትንም በማሰብ እስከ 16 ቀን እንዲጾም ተደርጎ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ምእመናንም ይህንኑ መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ሕፃን አዋቂው ሳይቀር የእመቤታችን ፍቅር አድሮባቸው ይጾማሉ፣ ያስቀድሳሉ፤ ይቆርባሉ፡፡
የፍልሰታን ጾም ሕፃን አዋቂው ይጾመዋል ከሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ የተለየ የሚያደርገው ምስጢሩ ምን ይሆን?የሚል ነበርና ለዚህም መምህር ደጉ ዓለም ካሣ መልስ አላቸው፡፡ «ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት ሀገር በመሆኗና ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ስላላቸው ምእመናን መሬት ላይ እየተኙና ጥሬ እየበሉ በሰላም በፍቅር ይጾሙታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ፍልሰታን ሳይጨምር ትልቅ ጾም የሚባሉት ዐቢይ ጾም፣ ነነዌ፣ ገሃድ/ጋድ/፣ ረቡዕና ዓርብ እና አጽዋማት ናቸው፡፡ ምእመናን ግን ፍልሰታን ከእነዚህ አስበልጠው መሬት ላይ እየተኙ ይጾሙታል፡፡ ይህ ደግሞ የእመቤታችን ፍቅር ስቧቸውና ኢትዮጵያም በእመቤታችን ፍቅር የተነደፈ ክርስቲያን ያለባት ሀገር በመሆኗ ነው፡፡»
ቀሲስ ስንታየሁ አባተ እንደዚሁ የተናገሩት ይህንኑ አባባል የሚያጠናክርና የሚያጎላ ነው፡፡ እንደሳቸው አባባል «በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፍልሰታ ጾም ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ይህም ከእመቤታችን ጋር ያለን ትስስር ሲሆን ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት ሀገር ናት፡፡ እመቤታችን በስደቷ ጊዜ ልጇ ወዳጇን መድኃኔዓለምን ይዛ በተሰደደችበት ሰዓት ያረፈችው በግብጽ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድርም መጥታ ዐርፋለች፡፡ በዚህ ጊዜ አራቱንም የሀገሪቱን መዓዘን ባርካለች፡፡
በዚህም ሊቃውንቱ እንደሚያስተምሩ ነቢዩ እንባቆም «የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ» ብሎ ተናግሮ የነበረው ትንቢት እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችበት ዘመን እንደተፈጸመ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሥርዓት አድርገን ፍልሰታን በልዩ ሁኔታ እንጾማለን» ነበር ያሉት፡፡
ድርሳነ ዑራኤል የሚለው መጽሐፍ በመግለጫው ላይ የተሰጠውን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡ «እመቤታችን ድንግል ማርያም በስደቷ ወራት ልጅን ሕፃኑ ኢየሱስን ይዛ ከምድረ እስራኤል ወደ ምድረ ግብጽ ከዚያም ወደ ብሔረ ኢትዮጵያ መጥታ በቅዱስ ዑራኤል መሪነት በደብረ ዳሞ በትግራይ፣ በጎንደር፣ በአክሱም፣ በደብረ ዐባይ፣ በጎጃምና በጣና በአደረገችው የስደት ጎዞ ሕፃኑ ኢየሱስ ለድንግል እናቱ ኢትዮጵያን ዓሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ» በማለት በሸዋና በወሎ፣ በሐረርጌና በአርሲ፣ በሲዳማና በባሌ፣ በከፋና በኢሉባቦር፣ በወለጋና በሌሎችም በኢትዮጵያ ክፍላተ አኅጉር በብሩህ ደመና ተጭነው በአየር እየተዘዋወሩ ተራራውንና ወንዙን /አፍላጋቱን/ እንዳስጎበኛት ይኸው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅቱ የፍልሰታ ጾም የሚጀምርበት በመሆኑ ምእመናን ምን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው? ከገቡስ በኋላ ምን ነገር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል?የሚለው ከጥያቄዎቻችን መካከል አንዱ ነበር፡፡ መምህር ደጉ ዓለም እንዲህ በማለት አመልክተዋል፡፡ ምእመናን ጾም /ሱባኤ/ ከመግባታቸው በፊት የሥጋን ኮተት ሁሉ አስወግደው መግባት አለባቸው፡፡ ሐሳባቸው ሁሉ ወደተለያየ አቅጣጫ ሳይከፋፈል ልቡናቸውን ሰብስበው ለአንድ እምነት መቆም፣ ከሱባኤ የሚያቋርጣቸውን አስቀድሞ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከገቡም በኋላ ሥጋቸውን ማድከም፣ በጾም በጸሎት መጠመድ አለባቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር እንደተሰጣቸው ጸጋ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ተገቢ ነው፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው ደካሞችን በመርዳት፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ አቅሙ የደከመና መርዳት የማይችል ደግሞ በምክርና ሐሳብ በማበርከት የበኩሉን ድርሻ ይወጣ፡፡ ብዙ ከመብላት ጥቂትን፣ ብዙ የሚያሰክር ጠጥቶ ከመንገዳገድ ውኃን ብቻ በመጎንጨት ለቁመተ ሥጋ የሚያበቃቸውን እያደረጉ ፈጣሪያቸውን ይጠይቁ፡፡ አለባበስን በተመለከተ ደግሞ አግባብና ወግ ያለው አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሌላው የተለየና የሌሎችን ቀልብ የሚስብ ወይም ልብስ መሆን የለበትም፡፡
ቀሲስ ስንታየሁ አባተ የተናገሩትም ከመምህር ደጉ የተለየ አይደለም፤ የእሳቸውን ሐሳብ የሚጋራ እንጂ፡፡ «እኛ የምንጾመው የወገኖቻችንን፣ በአጠቃላይ የሰውን ልጅ ጥፋት አታሳየን ብሎ ቦታና ጊዜ ወስኖ ሱባኤ የምንይዝበት ነው፡፡ ጾም ማለት ለእግዚአብሔር ማመልከቻ ማስገባት ማለት ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች ሦስት ቀን ጾሙ፣ በሦስት ቀናት ውስጥ ሀገራቸው ከመከራ ዳነች፡፡ እኛ በገዳማት ውስጥ ከ250 ቀናት በላይ እንጾማለን፡፡ ነገር ግን ስንጾም ማየት የሚገቡን ነገር አለ፡፡ «ፍቅር እንደሸማ ያላብስህ» እንደሚባለው ስንጾም ፍቅር ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾም ያለ ፍቅር፤ ፍቅር ያለ ጾም ዋጋ የለውም፡፡ ቁም ነገሩ እኛ በጾም ደርቆ መዋል ሳይሆን ፍቅርና ሰላም መታከል አለበት፡፡ የተጣላ መታረቅ አለበት፣ በቅዳሴ ሰዓት ቦታ ላጡ ቦታ መስጠት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ በተለይ አረጋውያንንና ሕፃናትን መደገፍ የወጣቶች ድርሻ ነው፡፡ በቅዳሴ ሰዓት የበረታው ለደከመው ቦታ መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሐሜትና ሁካታ ቂም በቀል ቦታ ሊኖረው አይገባም በማለት ተናግረዋል፡፡
እንደ ቀሲስ ስንታየሁ ገለጻ ጾም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ከሆነ ለምንድን ነው በጾማችን፣ በጸሎታችን ኅብረተሰባችን ከጉስቁልና ያልወጣው?ብለን ብንጠይቅ ሳይጾም ሳይጸለይ ቀርቶ ሳይሆን ፍቅር ስለሌለ ነው፤ እንጂ እግዚአብሔር ሳይሰማ ቀርቶ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ፊትም አሁንም ሆነ ወደፊት ይሰማል፡፡
በመጨረሻ ለመምህር ደጉ ዓለምና ለቀሲስ ስንታየሁ አባተ ያነሳንላቸው ጥያቄ አንዳንድ ሰዎች ታመው ከሕመማቸው እንዲፈወሱ፣ ስለ ማኅበራዊ ጉዳይ ሱባኤ በመግባት ራእይ ማየት አለብኝ ይላሉ፡፡ ራእይ ያላዩ ተስፋ እንዳይቆርጡ ምን ትመክራላችሁ?የሚል ነበር፡፡መምህር ደጉ «ምንም እንኳን ወሩ ከሌለው በተለየ የሱባኤና የራእይ ወቅት ሆኖ ቢገለጽም በፍልሰታ ጾም ራእይ ማየት አለማየት የሚለው የብቃት መለኪያ /ማረጋገጫ/ መሆን የለበትም፡፡ ቦታ ቀይረውና ከሰው ተለይተው በጾም በጸሎት መጠየቅ ታዝዟል፡፡ ኢትዮጵያን ምእመናን ወደ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንጠይቅ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ካልተሳካላቸው በተለያየ ጊዜ በሱባኤው ይቀጥላሉ እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለባቸው» ሲሉ መክረዋል፡፡
ቀሲስ ስንታየሁ በበኩላቸው «አንድ ሰው የሚጾመው ራዕይ ልይ ብሎ አይደለም፡፡ ይህ እግዚአብሔር በፈቀድ የሚታይ ነገር ነው፡፡ አባቶቻችን ሲጾሙ ሲጸልዩ ኃጢአታቸው እንዲገለጽላቸው እንጂ እግዚአብሔር እንዲገልጽላቸው አይደለም፡፡ አንተ ኃጢያትህ ከተገለጸልህና ንስሐ ከገባህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ፡፡ አንድ ሰው በኃጢአት ተሞልቶ እግዚአብሔርን ልይ ቢል ሊሆን አይችልም፡፡ እኛንና እግዚአብሔርን የሚለያየን ኃጢአትና በደል ነው፡፡ ስለዚህ የሚያራርቀንን ነገር ለማስወገድ መጾም አለብን፡፡ ምእመናን በሕይወታቸው ውስጥ ስላለው ችግር፣ ለሰው ልጅና ለሀገር የሚበጅ ነገር አምጣልን ብለው ሱባኤ በመያዝ መጾም መጸለይ የሚገባ ነው» በማለት መንፈሳዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያህል ምእመናን በሚጾሙበት ወቅት የተራቡትንና የታረዙትን በማሰብ ካላቸው ላይ ከፍለው ማብላትና ማልበስ ተገቢ ነው፡፡ ምእመናን ይህን የሚያደርጉት በፍልሰታ ወይም በሌሎችም አጽዋማት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሌላም ጊዜ እንደሆነ ያነጋገርናቸው እንግዶች አስረግጠው የተናገሩት፡፡ መርዳት መረዳዳት የኢትዮጵያዊነት ባህል ብቻ ሳይሆን የሃይማኖታችን መንፈሳዊ ግዴታችን ነው እያልን ጾሙን በሰላም በፍቅር አስጀምሮ እስከሚያስፈጽመን ድረስ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን አሜን፡፡ ወስብሐት ለ
እግዚአብሔር
Monday, June 28, 2010 8:05:40 PM
ሰኔ 20 እና 21 በእመቤታችን ስም በፊልጵስዩስ የታነጸችው የቤተክርስቲያን መታሰቢያ በዓል ነው[/B][/COLOR]
፡፡ ይህች ሃገር ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ተዘዋውረው ያስተማሩባትና ብዙ ምዕመናንን ያፈሩባት ቦታ ናት፡፡ ከዚያም በኋላ በዚህች ቦታ የመጀመሪያዋ በእመቤታችን ስም የታነጸች ቤተ ክርስቲያን መተከሏን የሰኔ 20 ስንክሳርና ሌሎችም ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ምሥጢራዊ /mystical/ መልዕክቶች ከብዙ በጥቂቱ ማብራራት ነው፡፡ እያንዳንዱ ምዕመን እንደ ጥረቱና እንደ መንፈሳዊ እይታው ብዙ ድንቅ መልዕክቶችን ቢያገኝም ከብዙ ጥቂቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ማኅበረ ምዕመናን
በግእዝና በአማርኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ቤተ ክርስቲያን» ተብሎ ተተርጉሞ የምናገኘው «አቅሌስያ» የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «የኅሩያነ እግዚአብሔር፣ የምዕምናን አንድነት» ማለት ነው፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህ ስም ከማኅበረ ምዕመናን በተጨማሪ ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም ይሰጣል፡፡ ይህም ሐዋርያዊ ትውፊት ነው፡፡ በሐዋርያት ዘመን ምዕምናን የሚገናኙበት ቤትም ፣ የምዕምናኑ አንድነትም «ቤተ ክርስቲያን» እየተባለ ይጠራ ነበር /ሮሜ 16.5፣ 1ቆሮ. 11.8/፡፡ ዛሬም ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ትውፊት ጠብቃ ሕንፃውንም ማኅበረ ክርስቲያኑም «ቤተ ክርስቲያን» እያለች ትጠራለች፡፡
የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሕይወት ረቂቅና ምጡቅ፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመረመር ሰማያዊ ነው፡፡ /1ኛቆሮ. 2.6-13/፡፡ ይህንን ረቂቅና ሰማያዊ ምሥጢር በተለያየ መንገድ ለትውልድ ማስተላለፍ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጠንካራ ስራና መንፈሳዊ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ አበው ይህን የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ከሚያስተላልፉበት መንገድ ዋነኛው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የሚገለጥ የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ
1. የቤተ ክርስቲያን ሰማያዊና ምድራዊ ባሕርያት
በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን ምድራዊም ሰማያዊም ገጽታ አላት፡፡ በአንድ በኩል ገና ጉዞዋን ያልጨረሰች፣ በምድር ላይ የሚኖሩና ለዚህም መብላት፣ መጠጣት የሚያስፈልጋቸው መድከም፣ መታመም. . .ያለባቸው አባላት ሕብረት ነች፡፡ ክርስቲያኖች ስቃይ፣ መከራ፣ ተጋድሎ የሚደርስባቸው በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ነው፡፡ /ራዕ. 21.4/፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ዕድገት የእግዚአብሔርም የሰውም ድርሻ አለበት፡፡ ሰዎች ይሰራሉ፤ እግዚአብሔር ስራቸውን ይባርካል፡፡ አገልጋዮች ሰዎች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ድካማቸውን አይቶ የሰዎችን ልብ ወደርሱ ይመልሳል፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች ይጀምራሉ፤ እግዚአብሔር ይፈጽማል፡፡ ሰዎች ይተክላሉ እርሱ ያሳድጋል።
ነገር ግን በምድር የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከላይ የተጠቀሱትን ምድራዊ ሥራዎችን ይሰራሉ ማለት ሰማያውያን አይደሉም ማለት አይደለም፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን በምድር ላይ በጉዞ ያለች በመሆኗ ምድራዊ ገጽታ ቢኖራትም ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳኑ ጋር ባላት ኅብረት ደግሞ ሰማያዊት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ አምልኮዎቿ /በቅዳሴዋ፣ በኅብረት ጸሎቶቿ. . ./ እንዲሁም እያንዳንዱ ምዕመን ባለው ሰማያዊ ሕይወት ምክንያት ከሰማያት ጋር ግንኙነት አላት፡፡ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት በሰማያዊ ተስፋ የጸና እና የዚህን ምድር ኑሮ እንደመጻተኝነት የሚቆጥር ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» እንዲል /ፊል. 3.20/
እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ሁለት ባሕርያት በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይገለጣሉ፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያነንን የሚሰሩት ሰዎች በመሆናቸው ሕንፃው የሰው ሥራ ቢሆንም፣ ቤተ ክርስቲያኑ ተሰርቶ በሜሮን ከከበረ በኋላ ግን የእግዚአብሔር ቤት፣ ሰማያዊ መቅደስ፣ የመላዕክትና የቅዱሳን ቤት ይባላል እንጂ እንደተራ ቤት አይቆጠርም፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን እና ነዋያተ ቅዱሳትን በቅብዓ ሜሮን ማክበር የማይቀር ሥርዓት ነው፤ ይህ ሥርዓት ቤቱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰማያዊ ቤት፣ የእግዚአብሔርና የቅዱሳን ማደሪያ የሚሆንበት ነው፡፡ በአጠቃላይ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ሰዎች ምድራዊ ቤት ይሰራሉ፤ እግዚአብሔር ሰማያዊ ያደርጋል፤ ሰዎች ባላቸው ጉልበትና ቁስ ቤት ሰርተው ለእግዚአብሔር ያስረክባሉ፤ እግዚአብሔር ደግሞ ደስ ይሰኙባት ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰማያዊት ቤት አድርጎ ይሰጣል፡፡ የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን መታነጽ በሚታሰብበት ዕለት /ሰኔ 20/ የሚዘመረው የቅዱስ ያሬድ ዜማም እንዲህ በማለት ይህንኑ ይገልጣል «ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን፤ ወሣረርዋ በመንፈስ ቅዱስ፤ ከመ ትኩን አርአያ ዘበሰማያት . . . ጊሡ ኀቤሃ፤ እስመ ኃይለ እግዚአብሔር ላዕሌሃ . . . ለዛቲ ቤተ ሣረራ አብ ቀዲሙ፣ ለዛቲ ቤት ሐነፃ ወልድ፤ ለዛቲ ቤት ወፈጸማ መንፈስ ቅዱስ. . . ሐነፀ መቅደሶ በአርያም፣ ቤተ ክርስቲያንን አነጿት /ገነቧት/፤ በሰማይ ላለችው አርአያ ትሆን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ መሰረቷት. . . ወደርሷ ገስግሱ፤ የእግዚአብሔር ኃይል በላይዋ ነውና . . . ያችን ቤት አብ አስቀድሞ መሠረታት፣ ያችን ቤት ወልድ አነፃት፣ ያችን ቤት መንፈስ ቅዱሰ ፈጸማት. . . መቅደሱን በልዕልና አነጸ»፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመጀመሪያ. . . ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን. . . ቤተ ክርስቲያንን አነጿት ብሎ የሰዎችን ድርሻ ከገለጠ በኋላ ይህችን ቤት አብ መሠረታት፣. . . ወልድ አነፃት፣. . . መንፈስ ቅዱሰ ፈጸማት ብሎ፣ የእግዚአብሔርን ድርሻ ገለጸ።
ከላይ ባየነው መልኩ የቤተ ክርስቲያን ሰማያዊና ምድራዊ ገጽታ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም ይንጸባረቃል፡፡ ስለዚህም ሁለቱም /ሕንፃው እና የምዕመናን ህብረት/ ምድራዊያን ስንላቸው ሰማያውያን፣ ሰማያውያን ስንላቸው ደግሞ በምድር ያሉ ናቸው፡፡
2. ድንጋዮች ተደራርበው የተሰራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን አንድነት የተገነባች ቤተ ክርስቲያን ይገልጣል፡፡
ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ከድንጋይ መስራት የተለመደ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ነው፡፡ ብዙ ድንጋይ በማይገኝባቸው የገጠር አካባቢዎች እንኳ ምዕመናን ከሌላ ቦታ አምጥተው በድንጋይ ያንፃሉ እንጂ በእንጨት ብቻ መስራት የተለመደ አይደለም፡፡ በድንጋይ መታነጹም ታላቅ ምሳሌያዊ ዋጋ ስላለው ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ምዕመናንን ሕያዋን ድንጋዮች፣ ጌታን የማዕዘን ራስ፣ ሐዋርያትና ነቢያትን መሰረት፣ ቤተ ክርስቲያንን /ማኅበረ ምዕመናንን/ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠራቸዋል፡፡ የመጀመሪዋ ቤተ ክርስቲያን በእመቤታችን ስም የታነጸችበት የመታሰቢያ በዓል ሲከበር በቅዳሴ ጊዜ የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት «እንግዲያውስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡ በሐዋርያና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፣ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንፃ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ» በማለት ያብራራል፡፡ /ኤፌ. 2.19-22/ የዕለቱ የቅዱስ ጴጥሮስ መልዕክትም የሚነግረን ይህንኑ ነው «በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መስዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንዲሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» /1ኛጴጥ. 2.4-6/፡፡ ወንጌሉም «አንተ አለት ነህ ፣ በዚህም አለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን አንጻለሁ» በማለት ይህንኑ ምሥጢር ይገልጣል፡፡ /ማቴ. 16.13-19/፡፡
ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ በሩንም፣ ድንጋዩንም መሳማችን ትውፊታዊ ነው፡፡ ይህም አንዳንዶች እንደሚሉት ከየዋሕነትና ክብርን ለማይገባ የመስጠት ዝንባሌ ስላለን ነውን? አይደለም፤ በነዚሀ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አካላት የክርስቶስ አካል የሆነችዋን ቤተ ክርስቲያን /በክርስቶስ አንድ አካል የሆኑ ምዕመናን ሕብረት/ የምናይበት ውሰጣዊ አይን /በቅዱስ ኤፍሬም አገላለጽ ብሩህ አይን /luminous eye/ ስላለን ነው፡፡ ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፀጋ ነው፡፡
3. ቤተ ክርስቲያን ወደ መንግሥተ ሰማያት ጉዞ የምታደርግ መሆኗና መንግስተ ሰማያት በመካከላችን መሆኗ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይገለጣል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በጉዞ ላይ ነች፡፡ በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን በምድረ በዳ ሲጓዙ በነበሩት ሕዝበ እስራኤል ትመስላለች፡፡ ደብተራ ኦሪት ከምድረ በዳ ጀምራ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እስከሰራበት ዘመን ድረስ በጉዞ ላይ ነበረች፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ጉዞዋን ጨርሳ እስክታርፍ ድረስ በጉዞ ላይ ነች፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ገልጦታል «እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፣ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ፡፡ እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲናፍቁ ያመለክታሉና፡፡ ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና፡፡» /ዕብ. 11.13-16/ ፡፡
ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ወደ መንግሥተ ሰማያት የምትጓዝ ብቻ ሳይሆን መንግስተ ሰማያት በመካከሏ የሆነች /ሉቃ. 16.21/ እግዚአብሔር በምዕምናን መካከል የሚገኝባት የመንግሥተ ሰማያት አረቦን /ቀብድ/ ናት፡፡ የመንግሥተ ሰማያት ደስታዋና ሁሉም ነገሯ እግዚአብሔር በምዕመናን መካከል መገኘቱ ነው /ራዕ. 21.3-4/። በእያንዳንዱ ቅዳሴ፣ ጸሎት፣ የምዕመናን አንድነት ሁሉ እግዚአብሔር ይገኛልና /ማቴ. 28.19-20/ ቤተ ክርስቲያን የመንግስተ ሰማያት አረቦን ናት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን «ሊመጣ ያለውን ዓለም ኃይል የቀመሱ» የሚላቸው /ዕብ. 6.5/
እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ሁለት ገጽታዎች በሕንፃው ይገለጣሉ፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ትውፊት በቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አውልጥቶ /with west to east orientation/ ይሰራል፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያንን «ምሥራቃዊ ጉዞ» ያመለክታል፤ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ባህር ወደ ምሥራቅ /ወደ መንግስተ ሰማያት/ የምትቀዝፍ መርከብ ናት /1ኛጴጥ. 3.20/፡፡ ይህም የገነት ምሳሌ ነው «እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔደን ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው» እንዲል /ዘፍ. 2.8/፡፡ ነገር ግን ወደ ምሥራቅ ስንዞር ፊት ለፊት የምናገኘው መሰዊያውን ነው፡፡ በእውነትም ቤተ ክርሰቲያን ከዕፀ ሕይወት /በመሰዊያው ላይ ካለው የጌታ ስጋና ደም/ የምንበላባት የደስታ ገነታችን ናት፡፡ ስለዚህ ወደ ምስራቅ መዞራችን የጉዟችን አቅጣጫ ሲያመለክት መሰዊያው በመካከላችን መሆኑ ደግሞ መድረሻችን ቀብድ ሆና በመካከላችን መገኘቷን ያመለክታል፡፡
4. ቤተ ክርስቲያን የዓለም ብርሃን መሆኗ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተገልጧል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ብርሃን እግዚአብሔር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምሳል ስለሆነችው ኢየሩሳሌም ሰማያዊት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል «ለከተማይቱ የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት፣ መብራትዋም በጉ ስለሆነ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም ነበር፡፡ አሕዛብም በብርሃኗ ይመላለሳሉ፡፡ /ራዕ. 21.23/ ነቢዩ ኢሳይያስም አስቀድሞ በትንቢቱ «ብርሃንሽ መጥቷልና፣ የእግዚአብሔር ክብር ወጥቶልሻልና ተነሽ አብሪ፡፡ እነሆ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታም ወደ መውጫሽ ፀዳል ይመጣሉ» ብሎ ስለ ቤተ ክርስቲያን /ጽዮን/ ተናግሯል፡፡ /ኢሳ. 60.1/ ይህን የእግዚአብሔርን ብርሃን ተቀብላ ብርሃን የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የዓለም ብርሃን /ማቴ 5፥24/።
ይህ የቤተ ክርስቲያን ብርሃንነት በሕንፃዋ ይገለጣል፡፡ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ከውጭ ወደ ውስጥ ለሚገባ ብርሃን ብዙም ትኩረት አይሰጥም፡፡ ይህም የጸሐይ ብርሃን ተጠልቶ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃን እንደሆነችና ከጨለማው ዓለምም ብርሃንን እንደማትፈልግ ለማመልከት ነው። ኦርቶዶክሳዊው ትውፊት በጧፍና በመብራት /በቀንዲል/ ቤተ ክርስቲያንን በብርሃን ማስጌጥ ነው፡፡ ቀንዲል በዘይት የሚበራ መብራት ነው፡፡ ዘይት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው /1ኛዮሐ. 2.27/፡፡ ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ በክርስቲያኖች ላይ የሚያበራ የልቦና ብርሃንን ያመለከታል። ይህ የልቦና ብርሃንም እግዚአብሔርን የማወቅ፣ ሰማያዊውን የእግዚአብሔር ክብር በልቦና የማየት፣ በአጠቃላይ በጨለማው ዓለም ውስጥ ከብርሃን አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፤ እግዚአብሔር ብርሃን ነውና፡፡ ይህንን ምሥጢር በዚህ በዓል /ሕንጸታ ቤተ ክርስቲያን/ የሚዘመረው የቅዱስ ያሬድ ዜማ እንዲህ ይገልጠዋል «ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን፤ ወሣረርዋ በመንፈስ ቅዱስ፤ ከመ ትኩን አርአያ ዘበሰማያት. . . ትበርህ እምከዋክብት. . . በጽድቁ ሐወፃ፤ እምነ ጸሐይ ይበርህ ገጻ፣ ቤተ ክርስቲያንን አነጿት፤ በመንፈስ ቅዱስም መሠረቷት፤ በሰማይ ላለችው አርአያ ትሆን ዘንድ. . . ከከዋክብት ይልቅ ታበራለች. . . በጽድቁ ጎብኝቷታል፤ ከጸሐይ ይልቅ ፊት ይበራል፡፡» በሌላም በተለያዩ ቦታዎች ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያንን «ትበርህ ከመ ኮከበ ጽባሕ፤ ወታስተርኢ ከመ ጎሕ፤ ንቁሐነ ንኩን ትጉሃነ ንጊሣ ለቤተ ክርስቲያን፤ እንደ ማለዳ ኮከብ ታበራለች፤ እንደ ጎሕም ትታያለች፤ ንቁዎች እንሁን፣ ተግተን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንገስግስ» ይላል፡፡
5. መስቀል ወደ ሰማይ የወጣንበት መሰላል መሆኑ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተገልጧል፡፡
የጌታ መስቀል ሰማይና ምድር የታሩቁበት፣ ምድራዊያን ወደ ሰማያት የደረሱበት መሰላል ነው፡፡ ይህንም ጌታ እንዲህ ብሎ ገልጦታል «ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ፡፡» /ዮሐ. 12.32/ ጌታ ከፍ ከፍ ባልኩ ጊዜ ማለቱ በመስቀል ላይ በወጣሁ ጊዜ ለማለት ነው፤ ሁሉን በፍቅሩ የሳበበት፣ ሞትን የሻረበት፣ ገነትን የከፈተበት፣ በአጠቃላይ ሰማይና ምድርን ያስታረቀው በመስቀሉ ነውና፡፡ በዚህ በዓል የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክትም «እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግርግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፣ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልን በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፣ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና፡፡ እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡» ይላል /ኤፌ. 3.19/፡፡ በአጠቃላይ በጌታ መስቀል እግዚአብሔርና ሰው ታርቀዋል፤ እግዚአብሔርና መላዕክቱ በሰዎች መካከል የሚገኙ ሆነዋል፤ ሰዎችም በምድር እንኳ ሆነው ልቦናቸው በሰማይ መኖር የሚችል ሆኗል፡፡
ይህ የመስቀል ምሥጢር በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የተገለጠ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትውፊት ቤተ ክርስቲያን ከጉልላቷ ጀመራ እስከ አጥር ቅጥሯ ድረስ በመስቀል ያጌጠች ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሰማያውያንና ምድራውያን የሚገናኙባት የእግዚአብሔር ቤት ናት ካልን፣ ይህን ያገኘችው በክርስቶስ መስቀል ነው፡፡ መስቀል የመንግሥተ ሰማያት መለኮታዊ አርማ ነው፡፡ ስለዚህ በሰማያት ላለችው ለኢየሩሳሌም አምሳል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን መስቀል አርማዋ፣ መለያዋ ነው፡፡ ስለዚህም የመስቀል፣ የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥተ ሰማያት ምሥጢር የተሰናሰለ ነው፡፡
በሌላም በኩል መስቀል የቤተ ክርስቲያን ኃይሏና ግርማዋ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስ «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና» እንዳለ፡፡ /1ቆሮ. 1.18/ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም በመስቀል ማጌጡ ኃይልንና ግርማን እንዲለብስ ያደርገዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ያሬድ በዕለቱ ዜማው «ጊሡ ሃቤሃ፤ እስመ ኃይለ እግዚአብሔር ላዕሌሃ፤ ወደርሷ ገስግሱ፤ የእግዚአብሔር ኃይል በላይዋ ነውና» በማለት ገልጾታል፡፡
በአጠቃላይ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የቤተክርስቲያንን ባሕርይ የሚያንጸባረቁ ብዙ ምሥጢራት ያሉት እንጂ በዘፈቀደ የሚሰራ አይደለም፡፡ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹ ሰዎችም /ባለሙያዎች/ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ትውፊታዊ ዕውቀት ያላቸው፣ እነርሱም ራሳቸው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቢሆኑ አባቶቻችን በዚህ መልኩ በትውፊት እንዲተላለፍ ያስቀመጡት መንፈሳዊ መልዕክት ተጠብቆ ለትውልድ ይተላለፋል፡፡
ይህም ደብተራ ኦሪትን ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር በመረጠው ሰው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሰው እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ብሏልና «እይ ፤ከአይሁድ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፣ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ፡፡ በሥራ ሁሉ ብልሃት፣ በጥበብም፣ በማስተዋልም በዕውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ. . .» /ዘጸ. 31.1-4/፡፡
አምላከ ቤተ ክርስቲያን አይለየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በዲ/ን በረከት አዝመራው
Sunday, May 30, 2010 3:00:05 PM
ንስር ንጉሠ አዕዋፍ ነው፤ በመብረርም ፈጣንና ጠንካራ የሆነ ነው፡፡ ረዥም ዘመን የሚኖር፣ ከሩቅ አጥርቶ የሚያይ፣ እስከ ተራሮች ከፍታና ከደመናት በላይ ለመብረር የሚያስችሉ ኃያላን አክናፍ ያሉት ነው፡፡ እንዲሁም ንስር ለጫጩቶቹ ርኅሩኅ ነው፡፡ በጥበብ ይንከባከባቸዋል ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙም ያለማምዳቸዋል፡፡
ከእነዚህ ተነጻጻሪ ባሕርያት የተነሣ እግዚአብሔር በትሕትና ራሱን ከንስር ጋር አመሳስሏል፡፡ እግዚአብሔር ዘላለማዊ፣ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን ተመልካች (ሁሉን የሚያይና የሚያውቅ የጥበብ ምንጭ)፣ ምሕረትን የተሞላ፣ ለሕዝቡ የሚራራና ወደ ድኅነት የሚመራቸው ነው፡፡
ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡን መርቶ ከግብፅ ባወጣቸውና ከፈርኦን ሠራዊት ጠብቆ በተአምር ቀይ ባሕርን ባሻገራቸው ጊዜ እንዲህ ብሏቸው ነበር፡- ‹‹በግብፃውያን ያደረግሁትን በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል›› (ዘጸ. 19፥4)፡፡
በንስር ሕይወት ውስጥ ካሉት ምሥጢራት አንዱ ሁልጊዜ ጎጆውን በከፍታ ላይ መሥራቱና በአለታማ ቋጥኞችና ምሽጎች ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለኢዮብ ጥበቡንና ኃይሉን ሲያሳየው ያለውን ልብ በሉ፤ ‹‹በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን? በገደል ላይ ይኖራል፤ በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል፡፡ በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጎበኛል፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች፡፡›› (ኢዮ.39፥27)
ንስር ስለምን ከፍ ብሎ ጎጆውን በተራሮች ጫፍ ላይ ይሠራል?[/B]
እንደ አዳኞችና አራዊት ያሉ ጠላቶቹ ሊደርሱበት ከማይችሉበት ስፍራ ለመገኘት ብሎ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ወደ ጎጆው ደርሶ ጫጩቶቹን ሊበላበት የሚችል ሌላ ጠላት አለ፡፡ ይህም ጠላት እስከዚያ ከፍታ ድረስ እስኪደርስ በልቡ ሊሳብ የሚችለው ዕባብ ነው፡፡
ታዲያ ይህንን ውስብስብ ችግር ንስር እንዴት ይፈታዋል?[/B]
ዕባቡ ዘልቆ እንዳይገባ ጎጆውን በመጠን ብዙ በሆኑ እሾኆች ከውጪ በኩል ያጥረዋል፡፡ የጎጆው ውስጠኛ ክፍል ደግሞ በላባዎች የተደራጀ ሞቃታማና ምቹ ነው፡፡ ውጪው ግን በእሾኽ የታጠረ ነው፡፡ ታላቁ ንስር ለጫጩቶቹ ጥሩ እንክብካቤ ያደርጋል፡፡ የሚበሉትን ያቀርብላቸዋል፤ በክንፎቹ እያንዣበበ ይጋርዳቸዋል፤ በአፉ (በመንቆሩ) ይመግባቸዋል፡፡ ትንንሾቹ አንስርት (ንስሮች) እንዳሻቸው እንዲኖሩ የተተዉ ቢሆኑ ኖሮ ለዘላለም ከጎጆአቸው ባልወጡ ነበር፡፡
ስለዚህ ጊዜው ደርሶ ጫጩቶቹ ሲያድጉ ታላቁ ንስር የመብረር ችሎታቸውን ይፈትናል፤ ጎጆውንም መትቶ ያነቃንቀዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መገፋቱ ጠንከር ሲል ጎጆው ከተራራው ጫፍ ወደ ዝቅተኛው ጫፍ ሊወድቅ ይችላል፡፡
ጎጆው በተነዋወጸ ጊዜ ከውጪ ያሉት እሾኾች ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በጫጩቶቹም ላይ መወጋትንና ሕመምን ያስከትላሉ፡፡ ክንፎቻቸውን ያንቀሳቅሳሉ ለመብረርም ይሞክራሉ፡፡ ከተሳካላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመብረርና ንጹሑን የሰማይ አየር እየተነፈሱ ለመደሰት ይችላሉ፤ ዳግመኛም ወደ ጎጆአቸው በፍጹም አይመለሱም፡፡ በዚህም ተልእኮውን በሚገባ ያለችግር በማከናወኑ ታላቁ ንስር ደስታ ይሰማዋል፡፡
የጫጩቶቹ የክንፋቸው ላባ በበቂ ሁኔታ ካላደገና መብረር ሳይቻላቸው ከወደቁ ታላቁ ንስር ፈጥኖ ክንፎቹን ዘርግቶ ይይዛቸዋል፤ በክንፎቹም ይሸከማቸዋል፡፡ ለተጨማሪ ቆይታም ወደ ጎጆአቸው ይመልሳቸዋል፡፡ ይህንን ዑደት መብረር እስከሚችሉ ድረስ ይደጋግመዋል፡፡ አይደንቅም ትላላችሁ?
‹‹ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፤ በክንፎቹ አዘላቸው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ብቻውን መራው››[/B] ዘዳ.33፥10
ከላይ እንደተገለጠው እግዚአብሔር ራሱን ከንስር ጋር አመሳስሏል፡፡ እኛም ከድንቅ ፍጥረቱ ከንስር ሕይወት አንዳንድ ቁም ነገሮችን እንቀስማለን፡፡
ምእመናን የንስር ጫጩቶችን ይመስላሉ![/B]
የንስር ጫጩቶች ደካሞችና በራሳቸው ለመቆምና በራሳቸው ለመኖር የማይችሉ ናቸው፡፡ የሰው ልጅም ሲወለድ በራሱ መብላት መጠጣት፣ መሄድ፣ መናገር፣ ማሰብ፣ ፍላጎቶቹን መፈጸም የማይችል ሆኖ ነው የሚወለደው፡፡ በተመሳሳይ በመንፈሳዊ ሕይወቱም ጠላቶቹን፣ ኃጢአትን፣ ሰይጣንን፣ የሥጋ ምኞትንና የዚህችን ዓለም መስህብነት ለመቃወም ደካማ ነው፡፡
ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ይህንን እውነታ ከአስከፊው ውድቀቱ በኋላ በስድስተኛው መዝሙሩ ሲገልጥ ‹‹አቤቱ በቊጣህ አትቅሠፈኝ በመዓትህም አትገሥጸኝ፡፡ ድዉይ ነኝና አቤቱ ማረኝ›› ብሏል፡፡ (መዝ.6፥1-2) የእግዚአብሔር ንቁ ዓይኖች፣ ኃያላን ክንዶቹና ሁልጊዜ በላያችን የሚጋርዱን ክንፎቹ ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን ደካማነታችንንና ኃጢአተኛነታችንን እስካላመንን ድረስ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ወደ እኛ ፈጽሞ አትመጣም፡፡
በሌላ ያማሩ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በሰማያት ላይ ለረድኤትህ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም፡፡ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው ፤ የዘላለም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፡፡››
(ዘዳ.33፥26)
የንስር ጫጩቶች እንደ እኛ አላዋቂዎች ናቸው፡፡ እኛ ከትምህርታችንና ከዲግሪዎቻችን ያገኘነው ምንም ይሁን ምን አላዋቂነታችንንና የእግዚአብሔር መሪነት እንደሚያስፈልገን ማመን ይገባናል፡፡ በመንፈሳዊው ዕይታ የሰው ልጅ አላዋቂ ነው፡፡ ወደፊት ስለሚመጣው ነገር፣ ከሞት በኋላም ስላለው ነገር፣ ሌላው ቀርቶ ስለ ራሱና በፍጥረታት ውስጥ ስላሉ በሚልዮኖች ስለሚቆጠሩ ነገሮች እንኳን አያውቅም፡፡ ማየት የማይችል ከመሆኑም የተነሣ የቃለ እግዚአብሔርና የመንፈስ ቅዱስ ብርሃንነት እንዲሁም ምክረ ካህን ያስፈልገዋል፡፡
እግዚአብሔር እኛን የሚንከባከብበት መንገድ ከንስር ጋር ይመሳሰላል![/B]
ንስር ከፍ ከፍ እንደሚልና ጎጆውን በከፍታ ላይ እንደሚሠራ እግዚአብሔርም ልጆቹ ከሌላው ሰው በተለየ መዓርግ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በቅድስና ሕይወት እንድንኖርና ከእርሱ ጋር ለዘላለም በመንግሥቱ ለመኖር ራሳችንን እንድናዘጋጅ ይፈልጋል፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት ከተወለድን ጀምሮ የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች ሆነናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፥20፡ ‹‹እኛ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› ብሏል፡፡ ከሰማያዊው አምላክ ተወልደናል፤ ምግባችን ቃለ እግዚአብሔርም፣ ሥጋ ወደሙም፣ ጸሎትና አንድነታችንም ሁሉም ከላይ ነው፡፡ ‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፤ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ›› (ያዕ.1፥18)፡፡
ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ›› (ቈላ. 3፥1-4)፡፡
እግዚአብሔር ጎጆአችንን በእሾኾች ያጥረዋል![/B]
በእርግጥ እግዚአብሔር ጥቂት እሾኾች እንዲያቆስሉን ያደርጋል፤ ይህም ፍቅሩንና ለእኛ ማሰቡን የሚያስረዳ ነው፡፡ በእሾኽ እንድንወጋ የሚፈቅደው በቁስላችን፣ በስቃያችንና በሕመማችን ስለሚደሰት አይደለም፤ በዚህ ስቃይ እንድናድግና እንድንጎለምስ ሊያስተምረንና ሊያለማምደን ነው እንጂ፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ስቃይና መከራ አልቀረለትም፤ እንዲያው በተገላቢጦሹ እስከ መጨረሻው መራራ ጽዋን ጠጣ፡፡ እንዲህ ተብሎ ስለ እርሱ እንደተጻፈ፡- ‹‹ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ (ዕብ. 5፥8)››
ሌሎችን የመፈወስ ጸጋ የተሰጠው ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ‹‹በሥጋው ላይ ስለነበረበት እሾኽ›› አቤቱታ አሰምቶ ነበር፡፡ እንዲህ ማለቱን ልብ በሉ፡ ‹‹ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መውጊያ ተሰጠኝ ይኸውም እንዳልታበይ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ፡፡ እርሱም ፡- ጸጋዬ ይበቃሃል ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ፡፡ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና›› (2ቆሮ. 12፥7-10)፡፡
‹‹ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው፡፡ ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና (ሮሜ. 8፥20-22)››
ስለዚህ እግዚአብሔር በእነዚህ እሾኾች እኛን በማሰቃየት ደስታን የሚያገኝ ሆኖ አይደለም፤ ይህ ለድኅነታችን አስፈላጊና ወሳኝ የሆነ ልንሸከመው የሚገባን መስቀል ስለሆነ ነው፡፡ ንስር ልጆቹን ከዕባብ ለመጠበቅ ጎጆውን በእሾኽ እንደሚያጥር እግዚአብሔርም ከቀደመው ዕባብ ከዲያብሎስ እጅ ይጠብቀን ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ ጥቂት እሾኾች እንዲኖሩ ይፈቅዳል፡፡ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ‹‹ለምን?›› ብለን እንጠይቀዋለን፡፡ እርሱም እንዲህ ሲል ይመልሳል፡- ‹‹እኔ የማደርገውን እናንተ አሁን አታውቁም በኋላ ግን ታስተውሉታላችሁ›› (ዮሐ.13፥7፣ መዝ. 72፣ ዕብ.12)፡፡
ንስር ጎጆውን እንደሚያናውጽ እግዚአብሔርም እንዲሁ ያደርጋል![/B]
እሾኾች ጫጩቶቹን ለመብረር እንዲገፋፉ ለማድረግ ሲል ንስር ጎጆውን ያነዋውጻል፡፡ ይህ ዓይነተኛ ፈተናና ትምህርት ነው፡፡ በእኛም እንዲሁ ነው፤ እግዚአብሔር ጎጆአችንን በኃይል ያነዋውጸዋል፤ ይሁናና በፍጹም አያፈርሰውም፡፡
ይህ ንውጽውጽታ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሣ ሊያስደነግጥ ይችላል፤ ይሁንና አትጨነቁ ዓላማውንም አትዘንጉ፡፡ እንድትበርሩ ሊያስገድዳችሁ ነው፤ አዎን በሰማያዊው ህዋ ደስ እንድትሰኙ ሊያደርግ ነው፡፡ በዘመናችን የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥና ዓውሎ ነፋስም የብዙዎችን ጎጆ የሚያናውጽና ሰዎችን ለንስሓ ለማዘጋጀት የሚደረግ የማንቂያ ጥሪ አንዳች ማሳያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በመንግሥቱ ለዘላለም የምንኖርበትን ዘላለማዊ ጎጆ አዘጋጅቶልናል፡፡ ስለዚህም ሰነፎችና ከዚህች ዓለም ጋር የተሳሰርን እንድንሆን አይፈልግም፡፡ ይህን ታላቅ ተስፋ በልባችሁ አኑሩ፤ ምድራዊ ስቃይን ሁሉ ትዘነጋላችሁ፡፡ ‹‹የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ›› በእናንተ ዘንድ እንዳለም አስታውሱ (ቈላ. 1፥27.)፡፡ ከዚህ ተግባር ጠቀሜታዎች አንዱ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔርን በመተማመን መጠባበቅንና ኃይልን ማደስን እንደ ንስር በክንፍ መውጣትን›› የምንማር መሆናችን ነው (ኢሳ. 40፥31)፡፡ እርሱ ‹‹መንግሥትህ ትምጣ›› ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል፡፡ እናም አንድ ቀን ወደ ሰማይ እንነጠቃለን፤ ወደ ምድራዊው ጎጆአችንም በፍጹም አንመለስም፡፡
ክንፎቹን ዘርግቶ ይሸከማቸዋል![/B]
መዝሙር 90 ይህንን እውነታ በሰፊው ያስረዳል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ፈጣን እርዳታ፣ ስለ መግቦቱ፣ ጥበቃውና አድኅኖቱ ይናገራል፡፡
‹‹በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል፡፡ … እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና፡፡ በላባዎቹም ይጋርድሃል፤ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል›› /መዝ. 90፥1-5/፡፡
ቀሲስ አውግስጢኖስ ሀና
ትርጉም ፡ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
Friday, May 14, 2010 9:27:13 PM
“ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን” [/COLOR][/B]/መዝ.46፥5/
ዲ/ን ዮሐንስ ልሳነወርቅ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማታ ማታ እየወጣ የሚያድርባት፣ሐሙስ ሌሊት በይሁዳ በኩል ለአይሁድ ተላልፎ የተሰጠባት፣ሐዋርያት ስለ ነገረ ምጽአት ጠይቀው የተረዱባት፣ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ጌታችን ያረገባት ተራራ -ደብረ ዘይት።
ዐርገ የሚለው የግዕዝ ግስ ዐረገ፣ወጣ በሚሉት የአማርኛ ቃላት የሚፈታ ሲሆን ዕርገት የሚለው ስምም ማረግን፣ መውጣትን፣አወጣጥን ያመለክታል።(አ.ኪ.ክ መ.ቃ)
አስቀድሞ ክቡር ዳዊት እንደተናገረው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱ እያዩት ወደ ሰማይ ዐርጓል። ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤ወእግዚእነ በቃለ ቀርን -እንዲል መዝ. 46፥5
ጌታችን በእውነት እንዳረገ ይኽም ሊታመን የማይችል እንዳልሆነ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያስረዳል።
ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሄደ፡ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፤ሥጋው አልተለወጠምና። ሃይ.አበው ዘዮሐ.አፈ.ክፍል 13 ቁጥር 15
አንቃዕድዎተ ዐይን
ወዘንተ እንዘ ይብሎሙ ተለዐለ ወነሥአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ እንዘ እሙንቱ ይኔጽሩ ኀቤሁ ወተሠወረ እምአዕይንቲሆሙ። የሐዋ. 1፥9
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ የወጣው በርህቀት(በመራቅ) እንጂ በርቀት (ቀ-ጠብቆ ይነበብ፤ረቂቅ በመሆን) አይደለም።ይኽም ማለት አስቀድሞ የተዋሐደውን ሥጋ አርቅቆ ፣ግዙፍነቱን አጥፍቶ ሳይሆን ከመለኮቱ ጋር በተዋሕዶ አንድ የሆነው ግዙፍ ሥጋ ግዝፈቱን ሳይለቅ ከዐይን በመራቅ፣ከፍ ከፍ በማለት፣ ወደ ሰማይ በመውጣት ነው።
በትምህርቱ የተጽናኑ፣በተአምራቱ የተማረኩ፣ ትዳራቸውን፣ ወላጆቻቸውን፣ ሃብታቸውን፣ ሥልጣናቸውን፣… የተዉለት ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር አብሮአቸው የቆየ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ሲለያቸው በናፍቆት ተይዘው ወደ ሰማይ ሲወጣ ትኩር ብለው ተመለከቱት። ያሳያቸውን ፍቅር፣ሑሩ ወመሃሩ በማለት ያዘዛቸውን አገልግሎት እንዴት እንደሚወጡት እያሰቡ ትኩር ብለው ተመለከቱት።
ነቢር በየማነ አብ
ነቢር በየማን -በቀኝ መቀመጥ በመጽሐፍ ቅዱስ አገባብ መሠረት ዕሪናን(በሥልጣን አንድ መሆንን) ያመለክታል።በመለኮቱ የእግዚአብሄር አብ ልጅ፣ በትስብእቱ(ሥጋን በመዋሐዱ) የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀመጠ።ማር.16፥19
ይኽ ስለ መለኮት የተነገረ አይደለም፤በመለኮቱስ ከአብ ሥልጣን ዝቅ ያለበት የዐይን ጥቅሻ ያህል ጊዜ የለምና።ነገር ግን ከተዋሕዶ በፊት ደካማ፣በደለኛ እና ውርደት ይስማማው የነበረው የእኛ ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ ጸጋን የሚያድል፣እውነተኛ ፍርድን የሚያደርግ፣ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ ነው።
ዕርገተ ልቡና
ሲጸልዩም ሆነ ሲናገሩ፣ሲጾሙም ሆነ ሲመገቡ፣ሲሠሩም ሆነ ሲያርፉ የአምላክዎን ውለታ በማሰብ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ለምን ያህል ደቂቃቆች ያርጋሉ(ይመሰጣሉ)?
ሐዋርያት ጌታችን በአካለ ሥጋ አብሮአቸው እያለ ያዘዛቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ በመታመን አደራቸውን እንደተገበሩ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ያለን ምዕመናንም ጌታችን በበረት በመወለድ፣የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ የሰጠንን የትሕትናን አደራ፤ወደ ግብፅ በመሰደድ፣በመስቀል በመቸንከር ያሳየንን መከራን የመቀበል አደራ፤አልአዛርን ከሙታን በማንሣት፣ራሱም በገዛ ሥልጣኑ ከሙታን በመነሣት የነገረንን ትንሣኤ ዘጉባኤን ተስፋ የማድረግ አደራ በሐሳባችን እያረግን ፣ልባችንን ከፍ ከፍ እያደረግን ክርስቲያናዊ ምግባራትን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረን በመያዝ ልንጠብቀው ይገባል።
በዕርገቱ ዕርገተ ልቡናን ያድለን።
Sunday, April 4, 2010 12:10:14 PM
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ... በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሠሮ ለሰይጣን ....................... አግዓዞ ለአዳም
ሰላም........................................... እምይእዜሰ
ኮነ ..................................... ፍስሐ ወሰላም::
ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሳ ........ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን
ሰይጣንን አሰረው ................ አዳምን ነጻ አወጣው
ሰላም ................................... ከእንግዲህ
ሆነ ........................................ ደስታና ሰላም
የትንሣኤው ትርጉም በዓሉና አከባበሩ
- «ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡
- መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
- «ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
- «ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡
- አንደኛው «ትንሣኤ» ኅሊና ነው፡፡ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር ነው፡፡
- ሁለተኛውም «ትንሣኤ» ልቡና ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡
- ሦስተኛው «ትንሣኤ» ለጊዜው የሙታን በሥጋ መነሣት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል፡፡
- አራተኛው «ትንሣኤ» የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ የእርሰ ትምህርታችንም መሠረት ይኸው እንደሆነ ይታወሳል፤ ብለን ተስፋ አናደርጋለን፡፡
- ዐምስተኛውና የመጨረሻው «የትንሣኤ» ደረጃም የባሕርይ አምላክ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «ትንሣኤ» መሠረት ያደረገ «ትንሣኤ ዘጉባኤ» ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡
- ወደተነሣንበት ዐላማ ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በቃሉም ምስጢር በይዘቱም ስለሚመሳሰሉ ጥላው ምሳሌውም፣ ስለሆነ «ፋሲካ» ተብሎ ይጠራል፡፡
- «ፋሲካ» ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ፌሳሕ» በጽርእ በግሪክኛው «ስኻ» ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ ዕድወት = ማዕዶት፣ በዓለ ናእት = የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ነጮቹ በእንግሊዝኛው «ስኦቨር» ይሉታል የዚህም ታሪካዊ መልእክቱ በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓል «ትንሣኤ» ተተክቶበታል፡፡
- ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ምእመናነ ክርስቶስ ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በእርሱ ትንሣኤ
- ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣
- ከኀሳር = ከውርደት ወደክብር፣
- ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣
- ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲሰ ሕይወት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡
- ክርስቲያኖች የትንሣኤን በዓል በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት ያከብሩታል፡፡ ስለዚህም ከበዓላት ሁሉ የበለጠ ሆኖ ይታያል፡፡
- መድኀኒታችን ሞትን በሞቱ ድል መትቶ፣ ስሙና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ የተነሣው መጋቢት 29 ቀን በ34 ዓ.ም እንደሆነ ታሪከ ቤተ ከርስቲያን ያስረዳል፡፡
- የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው በተነሡት ተከታዮቹ ምእመናን ነው፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዐቱ ይበዛ ይቀነስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ተቋርጦ አያውቅም፡፡ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን»
- ሲወርድ ሲወራረድ ከዚህ በደረሰው ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሕማማቱን ስታነብ ሰንብታ ለትንሣኤ እሑድ አጥቢያ ማታ በ2 ሰዓት «ለጸሎት ተሰብሰቡ» የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡
- ካህናቱ ተሰብስበው ሥርዐቱን በጸሎት ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም ይሰበሰባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንም ይሞላዋል፡፡
- ካህናቱ ሁሉ ለጸሎተ ፍትሐትም፣ ለሥርዐቱም መዝሙረ ዳዊት፣ ነቢያት፣ ሰሎሞንና ውዳሴ ማርያም ከደገሙ በኋላ «ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ» የሚለውን ግጥማዊ የደስታ መዝሙር ይዘምራሉ፡፡
- ቀጥሎም ምንባባቱና ሌላውም ሥርዐት ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ ዲያቆኑ «ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፣ ወከመ ኀያል ወኅዳገ ወይን፣ ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ = እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደተወው ኀያል ሰውም፣ ጠላቱን በኋላው ገደለ፡፡» የሚለውን የዳዊት መዝሙር ለመስበክ = ለመዘመር ነጭ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አክሊል ደፍቶ፣ የመጾር መስቀል ይዞ፣ እንደእርሱው ነጭ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ ደማቅ የጧፍ መብራት በሚያበሩና ድባብ = ጃንጥላ በያዙ ሁለት ዲያቆናት በግራ በቀኝ ታጅቦ ከመቅደስ ብቅ ብሎ በቅድስት ይቆማል፡፡ መዝ. 77-65 ይህም በጌታችን መቃብር በራስጌና በግርጌ በታዩት መላእክት ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ.20-12
- ዲያቆኑ ከላይ የተጠቀሰውን ምስባክ በረጅም ያሬዳዊ ዜማ በሰበከ ጊዜ ካህናቱ ከበሮ እየመቱና በእርጋታ እያጨበጨቡ ተቀብለው ይዘምራሉ፡፡
- ሕዝቡም የቻለው በዝማሬው ያለበለዚያም በጭብጨባና በልልታ የደስታ ዝማሬው ተሳታፊ ይሆናል፡፡ ይህ ምስባኩ በዲያቆኑ 2 ጊዜ በመላው ካህናትም 2 ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ዲያቆኑም መላው ካህናትም አንድ ጊዜ ብለው 5 ጊዜ ይሆናል፡፡ 5500 ዘመን ሲፈጸም በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ዓለም ለመዳኑ ምሳሌያዊ ማስረጃ ነው፡፡
- ቀጥሎም ካህኑ ትንሣኤውን የሚያበሥር ወንጌል ከማቴዎስ፣ ከማርቆስና ከሉቃስ አውጥቶ ያነባል፡፡ ከዮሐንስ ወንጌል ያለው የትንሣኤው ወንጌል ኋላ ለቅዳሴው ጊዜ ይቆያል፡፡ ዮሐ. 20-1-09
- በማስከተል የዲያቆኑን መስቀል ጨብጦ ከሊቃውንቱ መዘምራን ሥራው የሚመለከተው ወይም የተመደበው ባለሙያ መዘምር «ትንሣኤከ ለእለ አመነ» የሚለውን እስመ ለዓለም ከቃኘ በኋላ ለበዓሉ ተስማሚ የሆነው 2 አርያም ተመርቶ በመቋሚያ ይዘመማል፤ በማስከተልም «ዮም ፍሥሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን፣ እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ቀድሞ ተለይቶ ተነሥቷልና በሰንበተ ክርስቲያን ዛሬ ደስታ ሆነ፡፡...» የሚለውን አንገርጋሪ ያመለጥናል = ይመራል፡፡ በግራ በቀኝ እየተነሣ መዘምራኑም ይዘምሙታል ይጸፉታል፤ ያለዝቡታል፤ ወዲያውም «ብርሃነከ ፈኑ፤ ለእለአመነ = ለአመነው ብርሃንህን ላክልን፡፡» የሚለውን እስመ ለዓለም እየወረቡ መብራት እያበሩ ዑደት ያደርጋሉ = ቤተ ክርስቲያኑን በውስጥ ይዞራሉ፡፡
- በዚህ ጊዜ «በጨለማ የነበራችሁ ሕዝቦች ኑ የትንሣኤውን ብርሃን እዩ፣ ብርሃኑንም ወስዳችሁ የብርሃኑ ተካፋይ ሁኑ፡፡» እያለች ቅ/ቤተ ክርስቲያን ስታዘጋጅ የሰነበተችውን ጧፍ እያበራች ታድላቸዋለች፡፡ ሕዝቦቹም ካህናቱን ተከትለው በታላቅ ደስታና ድምቀት ዑደት ያደርጋሉ፡፡
- መዘምራኑና ካህናቱ ከዑደት ሲመለሱ «ይእቲ ማርያም» የተባለው የኪዳን ሰላም ይጸፋና ኪዳን ተደርሶ ሲያበቃ እንደ ቦታው ደረጃ ፓትርያርኩ ወይም ሊቀ ጳጳሱ ወይም ደግሞ አለቃው፣ ቆሞሱ፣ ካህኑ ዘለግ ባለ ድምፅ በንባብ «ክርስቶስ ተንሥአሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡» ሲል ካህናቱና መዘምራኑ በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን = በታላቅ ኀይልና ሥልጣን፡፡» ብለው ይቀበላሉ፡፡
- አሁንም ካህኑ «አሰሮ ለሰይጣን = ሰይጣንን አሰረው» ባለ ጊዜ መላው ካህናት «አግዐዞ ለአዳም = አዳምን ሐርነት ነጻነት አወጣው» ይላሉ፡፡ ቀጠል አድርጎ ቄሱ «ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት» ሲላቸው ሁሉም ካህናት «እምይእዜሰ = ከዛሬ ጀምሮ» ብለው ይቀበላሉ፡፡ ቄሱም «ኮነ ፍሥሐ ወሰላም = ሰላምና ደስታ ሆነ» ብሎ ሦስት ጊዜ ዐውጆ ሲያበቃ «ነዋ መስቀለ ሰላም» እያለ መስቀል ሲያሳልም ካህናትና ሕዝቡም «ዘተሰቅለ ቦቱ መድኀኔዓለም» እያሉ ይሳለማሉ፡፡ ካህኑም «እግዚአብሔር ይፍታ» ይላል፡፡ ግብረ ሕማማት ሲነበብበት ከሰነበተው ጠበልም ይረጫል፡፡ የተረፈውንም ጠበል ሕዝቡ ለበረከት ወደየቤቱ ይወስደዋል፡፡
- ከዚያም ልኡካኑ ለቅዳሴ እየተዘጋጁ ሊቃውንት መዘምራኑ ምስማክ መወድሱን ካዜሙ በኋላ በመቋሚያ ይዘምሙታል፡፡ አያይዞም በዓመት ሦስት ጊዜ የሚዘመረውን «ይትፌሣሕ» የተባለውን መዝሙር ቃኝተው ከዘመሙ በኋላ «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ = ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካውን ታደርጋለች፡፡» እያሉ ይጸነጽላሉ፡፡ አያይዘውም የመዝሙሩን ሰላም ይጸፋሉ፡፡
- ወዲያው መንፈቀ ሌሊት ሲሆን ቅዳሴ ተቀድሶ ይቆረባል፡፡ ከዚያም ዕጣነ ሞገር = በዕጣን ፈንታ ቅኔው ተቁሞ ሠርሖተ ሕዝብ = የሕዝብ ስንብት ከሆነ በኋላ ለመፈሰክ ሕዝቡ ወደየ ቤቱ ይሔዳል፡፡
- ሕዝቡ በየቤቱ፣ ካህናቱም ከቤተ ክርስቲያን በየአካባቢው ባህል በተለይ አክፋዮች መጀመሪያ ቅባት አጥቶ የሰነበተ ሆድ እንዲለሰልስ የተሞቀ የተልባ ጭልቃ ይጠጣና የሹሮ ወጥ በቅቤ፣ በአይብ፣ የበረታም በዶሮ ወጥ፣ ወይም በበግና በከብት ሥጋ ወጥ ይገድፋል፡፡
- በእርጎ፣ በአይብ የተደራረበ እንጀራ በግፍልፍል የሚገድፉም አሉ፡፡ በአንዳንድ የሰሜኑ ሀገራችን ደግሞ የተልባ፣ የኑግና የሱፍ ጭልቃ ከማር ጋር ታሽቶ ከተጠጣ በኋላ በእርጎ፣ በአይብ፣ በወተት፣ በቅቤና ድልህ በተቀባ እንጀራ ይገድፋሉ፡፡
- ሲነጋም ከጾሙ አጋማሽ ጀምሮ ወንዱ ለእርድ የሚሆነውን ሰንጋውን፣ ሲቀልብ፣ በጉን ፍየሉን ሲሞክት ዶሮውን ሲመርጥ፣ ሲገዛ ሲለውጥ፣ ሰንብቶ ነበርና በግልም በኅብረትም ያ ይታረዳል፡፡
- ሴቶችም ቅቤውን ሲያነጥሩ፣ በርበሬውን ሲደልሁ፣ ለእንጀራና ዳቦ የሚሆነውን ዱቄት ሲያዘጋጁ ለጠላ የሚሆነውንም እኸል ሲያሰናዱ አይቡን በልዩ ልዩ ቅመም መጣጣ ሲያደርጉና ባዶ ማለትም ወገሚት የተባለውን በሽንኩርት፣ በጤና አዳም፣ ጣዕሙ እንዳይለወጥ ሲቀምሙ ሰንብተው ዝግጅቱ ተከናውኖ ነበር፡፡
- ጧትም ይህ የመግደፊያ ዝግጅት በየቤታቸው ለሌላቸው ድኾች በየመንደሩ እየተዞረ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ» እየተባለ ከሥጋውም፣ ከአይቡም፣ ከቅቤውም ከመጣጣሙም፣ ከእርጐውም ይታደላል፡፡
- ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ» እየተባባለ በመጠራራት ዐብሮ ሲበላ ሲጠጣ ልዩ ልዩ ጨዋታ ሲጨዋወት ለንስሐ አባትና ለሽማግሌዎች ለወዳጅ ዘመድም የአክፋይ ዳቦ፣ ወይም የሥጋ ወጥ ግፍልፍል ሲወስድ ይሰነብታል፡፡
- ይህ በዚህ እንዳለ ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታት ሰሙነ ፋሲካ ወይም ትንሣኤ እየተባሉ የየራሳቸው ምስጢራዊ ስያሜ አላቸው፡፡ ይኸውም፡-
- ሰኞ = ጌታችን በሞትና ትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሆና «ፀአተ ሲኦል ማዕዶት» ትባላለች፡፡ ዮሐ. 19-18 ሮሜ. 5-10-17 የዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ግን ገበሬው፤ ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ሁሉ ሴቶቹ ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለሆነች «እጅ ማሟሻ» ሰኞ ትባላለች፡፡
- ማክሰኞ = የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ሐዋርያ አልነበረም ኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት እኔ ሳላይ አላምንም በማለቱ በዚህ ጥያቄው መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ ሆና ዕለቲቱ «በቶማስ» ተሰየመች፡፡ ዮሐ. 20-24-30
- ረቡዕ = ከሞተና ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላሥነሣው፣ አላዓዛር መታሰቢያ የእርሱንም ተነሥቶ በማየት በጌታችን ብዙ ሕዝብ ስለአመነበት ቀኒቱ «አላዓዛር» ተብላ ትታሰባለች፡፡ ዮሐ. 11-38-46
- ኀሙስ = ከላይ በጸሎተ ኀሙስ ሐተታ ላይ እንደተገለጸው የአዳም ተስፋው ተፈጽሞለት ከነልጅ ልጆቹ ወደቀደመ የገነት ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆና «የአዳም ኀሙስ» ተብላ ይኸው ትከበራለች፡፡ ሉቃ. 24-25-49
- ዐርብ = በክርስቶስ ደም ተዋጅታ በተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ በመሆኗ በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ዐርብ «ቤተ ክርስቲያን» ተብላ ትጠራለች፡፡ ማቴ. 26-26-29 የሐ. ሥራ. 20-28 ይህች ዕለትም እንደ ዕለተ ኀሙስ ሦስት ስያሜዎች አሏት፡፡ ይኸውም እንደኛው ከሆሳዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ የጌታችን አርብዓው ጾም የሚፈጸምባት የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት፣ በመሆኗ በቤተ ክርስተያን «ተጽዒኖ» ስትባል በሕዝቡም ዘንድ በሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤው ከባዱን ሥራ ስለሚያቆምባት «የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ» ትባላለች፡፡
- ሁለተኛውም በመጀመሪያ የሰው አባትና እናት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት፣ ኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም መከራ ተቀብሎ ስለተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለፈጸመባት «ዕለተ ስቅለት አማናዊቷ ዐርብ» ትባላለች፡፡
- ሦስተኛውም ይኸው በሰሙነ ትንሣኤው ያለችው ደግሞ «ቤተ ክርስቲያን» ትባላለች ማለት ነው፡፡
- ቀዳሚት = በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበይባት «የቁራ ገበያ» የገበያ ጥፊያ ስትባል በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ለአገለገሉት በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት፣ የትንሣኤው ዕለት ገና ከሌሊቱ ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው በመገሥገሣቸው ትንሣኤው ከሁሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አእንስት መልካም መታሰቢያ ሆና «አእንስት» ተብላ ትጠራለች፡፡ ሉቃ. 23-27-33፣ 24-1-01፣ ማቴ. 25-1-11
Tuesday, March 30, 2010 9:18:14 PM
በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት አሥራ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1. ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተኰርዖት›› የሚለው ቃል ኩርዐ - መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ርእስ ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ 27-24፤ ማር 15-15፤ ሉቃ 23-25፤ ዮሐ 18-39)፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው ራሱ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር 15-19)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾህ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የሆነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ ተንኮል የተጐነጐነ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡
2. ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተፀፍዖ›› የሚለው ቃል ፀፍዐ በጥፊ መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ መልታሕት ደግሞ ፊት ጉንጭ ማለት ነው፡፡
ጌታችን ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቆጥሮበት መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው ‹‹ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡ በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ 27-27)፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል (ዮሐ 19-2-4)፡፡ አላወቁትም እንጂ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት የዘለዓለም አምላክ ነው፡፡
3. ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)
ርኩሳን አይሁድ በብርሃናዊው የክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ሁኔታ ምራቃቸውን እንደተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ወሪቅ›› የሚለው ቃል ወረቀ ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም እንትፍ አለ፣ (ተፋ) ማለት ነው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ (ምዕራፍ 5ዐ-6) ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደተነገረ እየዘበቱበት ምራቃቸውን ተፉበት (ማቴ 27-29-3ዐ፤ ማር 15-19)፡፡ በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡ እንኳን በአምላክ ፊት በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ያስነውራል፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የሆነውን ምራቅ ተቀበለ፡፡
4. ሰትየ ሐሞት (መራራ ሐሞት መጠጣት)
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ተጠማሁ ባለ ጊዜ መራራ ሐሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ሰተየ›› ማለት ጠጣ ማለት ነው፡፡ ሐሞት የሚለውም አሞት ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ በመዝሙር 68 ቁጥር 21 ላይ ‹‹ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፣ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ›› ብሎ ነቢዩ ዳዊትን ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ ሆምጣጤ ተሞልቶበት ተቀምጦ ከነበረው ዕቃ ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው ወደ አፉ አቀረቡለት፡፡ ውኃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ 27-34)፡፡ ጌታችንም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ (ማቴ 27-48፤ ማር 15-36፤ ሉቃ 23-36፤ ዮሐ 19-29)፡፡
ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃ ምንጭ የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም (ኢሳ 55-1)፡፡ አርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ኳትነው ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከአለት ላይ ውኃ አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት (ዘዳ 16-1-2ዐ፤ 1ቆሮ 1ዐ-3)፡፡ የዝናማት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ሁሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፤ ሆምጣጣውንም ጠጣ፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ የመረረውን መጠጥ ተቀበለ፡፡
5. ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባው እስኪላጥ ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተቀሥፎ›› የሚለው ቃል ቀሠፈ- ገረፈ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ዘባን›› ደግሞ ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጠው የተገረፈ አይሰቀልም፡፡ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ጲላጣስ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገረፈው፡፡ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ብሎ ከታጠበ በኋላ ክርስቶስን ያለ ኃጢአቱ በመግረፍ ለአይሁድም አሳልፎ በመስጠት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንዲሉ የታጠበ እጁን መልሶ አቆሸሸው (ማቴ 27-28፤ ማር 15-15፤ ዮሐ19-1)፡፡
መድኃኒታችን መንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ተገረፈ፡፡ አይሁድ አገረ ገዥያቸው ጲላጣስ ላቀረበላቸው ምርጫ ይፈታላቸው ዘንድ ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን ክርስቶስን ሳይሆን ራሱን እንኳን ከምድራዊ ወህኒ ማውጣት ያልቻለውን ወንበዴውን በርባንን መረጡ፡፡ መገረፍ ይገባው የነበረ በርባን ተለቀቀ፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› (በኢሳ 5ዐ-6) ተብሎ እንደተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውንና የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው፡፡
6. ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተዐርቆተ›› ማለት ታረዘ፤ ተራቆተ ማለት ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ልብሱን ተገፍፎ ዕራቁቱን ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የጸጋ ሁሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡
የሲኦል ወታደሮች የሆኑት አጋንንት የሰውን ልጅ ጸጋ ገፍፈውት ነበርና ጲላጦስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ በሰጣቸው ሰዓት ወታደሮች ልብሱን ገፍፈውታል (ማቴ 27-27)፡፡ የሰው ልጅ ለቀረበለት ምርጫ የሰው ምላሽ ዘራፊው፤ ገራፊው ወንበዴ በርባን እንዲፈታለት ነበር፡፡ ‹‹አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ፣ ደይ እዴከ ኅበ ዘፈቀድከ! እነሆ እሳትና ውኃን አቅርቤልሃለሁ፣ እጅህን ወደ ፈቀድከው ስደድ›› ሲባል የሰው ልጅ እጁን ወደ እሳት ሰደደ፡፡
7. ርግዘተ ገቦ (ጎንን መወጋት)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር መወጋቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ርግዘት›› የሚለው ቃል ረገዘ- ወጋ ከተሰኘ የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ገቦ ማለት ደግሞ ጎን ማለት ነው፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አጠገብ፣ በግራና በቀኙ ሁለት ወንበዴዎች ተሰቅለው ነበር፡፡ ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር ጭናቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ አይሁድ ጲላጦስን በለመኑት መሠረት ጭፍሮቹ የሁለቱን ወንበዴዎች ጭን ጭናቸውን ከሰበሩ በኋላ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ፈጽሞ እንደሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፡፡ ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰ (ዮሐ 19-33)፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በሆነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለጣለው ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ?›› ተባለ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት ነበርና (1ቆሮ 15-54-55፤ ኢሳ 25-8፤ ሆሴ 13-14)፡፡
ከተወጋው የጌታችን ጎን ደምና ውኃ መፍሰሱም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘለዓለምን ሕይወት አጥቶ የነበረው ሰው ልጅነቱና ሕይወቱ እንደተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛልና (ዮሐ 3-5፤ ዮሐ 6-54)፡፡
8. ተአሥሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተአሥሮት›› የሚለው ቃል አሠረ (ሲነበብ ይላላል) ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አሠረ ማለት ነው፡፡ ‹‹ድኅሪት›› የሚለው ቃል ደግሞ ተድኅረ- ወደኋላ አለ ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለትና ሰዓት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል፡፡ አፍገምግመውታል (ዮሐ 18-12)፡፡
በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ይፈታ ዘንድ ሲል መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡
9. አምሥቱ ቅንዋተ መስቀል
መድኃኒታችን በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸውን ጠንካራ የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ቅንዋት›› የሚለው ቃል ቀነወ- ቸነከረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ መስቀል ማለት ደግሞ ዝም ብሎ የቆመ ግንድ ሳይሆን አሁን በየሥፍራው እንደምናየው ምልክት የተመሳቀለ እንጨት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቸነከረባቸው አምስቱ ችንካሮች ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፤ ሮዳስ ይባላሉ፡፡ እነዚህም የአምሥቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መሆናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡
ሐዋርያው ቶማስ ከትንሣኤ በኋላ ወንድሞቹ ሐዋርያት ስለ ትንሣኤው በነገሩት ጊዜ ‹‹የችንካሩን ምልክት በዓይኖቼ ካላየሁ፣ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላስገሁ፣ በእጄም የተወጋውን ጎኑን ካልዳሰስኩ አላምንም›› ማለቱ በብረት ቀኖት በመቸንከሩ ነበር (ዮሐ 2ዐ-25)፡፡ መድኃኒታችን በኃጢአት ቀኖት (ምስማር) ተይዞ የነበረውን ሰው ለማዳን በብረት ቀኖት ተቸነከረ፡፡
እንግዲህ አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የሚባሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ድሀ ያይደለ ጌታ፤ ፍጡር ያይደለ የፈጠረውን ሥጋ ገንዘብ ያደረገ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ብሎ ተናቀ፡፡ የሕማም ሰው፤ ደዌንም የሚያውቅ ሆነ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፡፡ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ይህም የሰውን ልጅ ለማዳን ማለትም እኛን ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰንና ከሕማመ ሥጋ ከሕማመ ነፍስ ሥቃይ ያሳርፈን ዘንድ ነው፡፡ ቁስለ ኃጢአታችንን ያደርቅልን ዘንድ ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፡፡ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ስለ በደላችን ደቀቀ፡፡ ሊያረጋጋን ተጨነቀ፡፡ ሊያሣርፈን ተሠቃየ፡፡ አፉንም አልከፈተም፡፡
የእግዚአብሔር የመሥዋዕቱ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ መልካምን እንጂ ግፍን አላደረገም ነበር፡፡ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ወሰብእ ወልድ ዋህድ ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ በተመረመረ ጊዜ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም፡፡ በፈቃዱ ነፍሱን ስለ እኛ መሥዋእት አደረገ፡፡ ፋሲካችን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሥጋውን ቆረሰልን፣ ደሙንም አፈሰሰልን (ኢሳ. 53-1-13፤ ዮሐ. 10-18፤ ዮሐ. 19-30፤ 1ኛቆሮ. 5-7)፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈረደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡›› ለኃጢአት ሞትን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን ተሸከመ፡፡ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ ብሏል (1ጴጥ.22-2-25)፡፡ ክርስቶስ የሞተልን ለጽድቅ ሞተን ለኃጢአት እንድንኖር አልነበረም፤ የኃጢአት ኑሮ እንዲያከትምልን እንጂ፡፡
እንግዲህ የእኛ ሕያውነትስ ለጽድቅ ይሆን ወይስ ለኃጢአት ዛሬ ሕይወታችንን መለስ ብለን ልናጤነው ሥጋዊ ፍላጎታችንንና የዓይን አምሮታችንን ክደን ነፍሳችንን ለማዳን መከራ መስቀሉን ተሸክመን ሕማማቱን እያሰብን ፈጣሪአችን ክርስቶስን ልንከተለው ይገባን ነበር (ማቴ.16-24)፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ትምክህታችን መስቀሉ ማለትም በመስቀሉ ላይ የተፈፀመው ቤዛነት መሆን አለበት፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽኑ መከራ ማለትም በመከራ ሥጋ ላይ መከራ ነፍስ፣ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም የተፈረደበትን ሰው ለማዳን ጽኑ መከራ ተቀበለ፡፡ የለበሰው ሥጋ መከራ የተፈረደበት ነበርና በዕፅ ምክንያት ወደ ዓለም የገባውን ኃጢአት ለማስወገድ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ የበለሲቱ ደም ፈስሷልና ክርስቶስ ደሙን አፈሰሰ፡፡ አዳም እጁን ዘርግቶ የበለሲቱን ደም ለማፍሰስ ደሙን አፈሰሰ፡፡ አዳም እጁን ዘርግቶ የበለሲቱን ደም ለማፍሰስ በእግሮቹ ወደዚያ ተጓዘ፡፡ ክርስቶስ ግን በእግሮቹ ወደ ቀራንዮ ተጉዞ እጆቹን ለቀኖት ዘርግቶ የራሱን ደም አፈሰሰ፡፡ በችንካርም ላይ ቆመ፡፡ አዳም የበለሲቱን ፍሬ ወደ አፉ አሰገብቶ አጣጣመ፡፡ ክርስቶስ ግን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፡፡ ሆምጣጤንም ጠጣ፡፡ አዳም የብርሃን ልብሱን ተገፍፎ ራቁቱን ቀረ፣ በበለስ ቅጠል ተሸፈነ፡፡ ክርስቶስ ግን ልብሱን ተገፍፎ ዕራቁቱን ተሰቀለ፡፡ ፀሐይም በመጨለሟ በጨለማ መጋረጃነት ተሸፈነ፡፡ ይልቁንም አዳም የተጎዳው በነፍሱ ነውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ክሶ ታረቀው፣ ከራሱም ጋር አስታረቀው፡፡
ዛሬ ግን ክርስቶስ አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል በትዕግሥት ተቀብሎ ኃጢአታችንን ካራገፈልን በኋላ በኃጢአት ሸክም ጎብጠን ተገኘን፡፡ ‹‹እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ›› በሚለው አምላካዊ ቃል ብንጠራም ጆሮ ዳባ ልበስ ብለናል፡፡ በመስቀሉ ደም ሰላም ሆኖልን ሳለ በጦርነት ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ ከታረቀን በኋላ ተጣላን፡፡ ከእርግማን ሲዋጀንም ዳግመኛ ከእርግማን በታች ወደቅን፡፡ የመስቀሉ ነገር በመስቀል ላይ የተፈጸመው ቤዛነት ሥጋ ወደሙን መቀበል መስቀል መሳለም በመስቀል ማማተብ የመስቀል ምልክት መያዝም ሞኝነት ሆነብን፡፡ በዚህ በመጨረሻው ዘመን የመስቀል ጠላቶች ሆነን ተመላለስን ሆዳችንን (ሥጋችንን) አመለክን፡፡ ነውር መሥራትን እንደክብር ቆጠርነው፡፡ ለሰማያዊ ክብር ባለቤትነት ከሞተልን በኋላ አሳባችን ምድራዊ ሆኖ ተገኘ (ማቴ.11-28፡፡1ቆሮ.1-18፡፡ ቆላ.1-18)፡፡
ዛሬም በእኛ እጅ ክርስቶስን የምናሳዝንበትንና የምናስቀይምበት የኃጢአትና የበደል መቃ አለ፡፡ ወገኖቻችንን በግፍ ቀንበር የምናደቅቃቸው፣ በግፍ በትር የምንቀጠቅጣቸው ከሆነ ይኸም ክርስቶስ ራሱን የተቀጠቀጠበት መቃ ነው፡፡ ምክንያቱም በታናናሾቻችን ላይ የምንፈጸመው ሁሉ በእሱ ላይ እንደተፈጸመ ይቆጠራልና፤ ሳውል ክርስቲያኖችን ባሳደደ ጊዜ ክርስቶስ በሰማይ ሆኖ ‹‹ለምን ታሳድደኛለህ›› ማለቱ ለዚህ ነው (የሐዋ.9-1-30)፡፡
ትናንት ክፉዎች አይሁድ በጥፊ እንደመቱት እኛም በዕደ ልቡናችን በክህደት ጥፊ እየመታነው ነው፡፡ እንደ አይሁድ እጆቻችንን ለበደል እየዘረጋን ነው፡፡ በጥፊ የመታህ ማነው? እወቅ እያሉ እንዳፌዙበት እኛም እግዚአብሔር እንደማያውቅ አድርገን በምንሠራው ሥራ እየቀለድንበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ካለ ለምን እንዲህ አያደርግም እያልን እያፌዝንበት ነው፡፡ ከኃጢአት ለመመለስ በደልን ለማራቅ ሳንወስን በፊቱ መንበርከክ ፌዝ ነው፡፡
ምን ያደርገኛል? ማንስ ምን ሆነ? በሚል ደካማ አስተሳሰብ በእግዚአብሔር ፊት የማይገባ ሥራ መሥራት እንደ አይሁድ በፊቱ ላይ መትፋት ነው፡፡ አይሁድ ቢንቁት አይደል በፊቱ ላይ የተፉት? እኛም ብንንቀው ነው በፊቱ ኃጢአት የምንሠራው፤ ምራቅ አስጸያፊ እንደሆነ ኃጢአትም አስጸያፊ ነው፡፡ እነዚያ ነውራቸውን እንደ መልካም እንዳዩት እኛም ነውር ኃጢአታችን መልካም ይመስለናል፡፡
ተጠማሁ ባለ ጊዜ ለመብሉ ሐሞት ለመጠጡ ሆምጣጤ አቀረቡለት፡፡ ትናንትና ዛሬ ለዘላለም ሕያው የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ጽድቅን ተርቦና ተጠምቶ ሳለ ምንድን ነው ያቀረብንለት? ሕይወታችን ጣፋጭ ነው? ወይስ መራራ? ዛሬ ያቀረብንለት መጠጥ የኃጢአትና የበደል መራራ ሆምጣጣ መጠጥን ነው፡፡ ይኽም የእግዚአብሔር ወዳጆች አለመሆናችንን ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ማንም ቢሆን ለወዳጁ የሚያቀርበው መራራውን ሳይሆን ጣፋጩን ነውና፤ መራራውን አሞት ቀምሶ የተወ አምላክ እኛንም ዓይቶ መርምሮ መራሮች ሆነን ካገኘን ለምረረ ገሃነም ይተወናል፡፡
የክፋት የምቀኝነት የግብዝነት የትዕቢት የአመንዝራነት አለንጋ በእጃችን ካለ ይኽም ክርስቶስ የተገረፈበት አለንጋ ነው፡፡ ክርስቶስን ካሳዘንነው ካስቆጣነው በክፉ ሥራችን በሐዘን በንዴት በቁጣ አለንጋ ገረፍነው ማለት ነው፡፡ ወገኖቻችንን የምንገርፍበትም የግፍ አለንጋ በእጃችን እስካለ ድረስ የዛሬዎቹ አይሁዳውያን እኛ ነን፡፡ እንደ ጲላጦስ ንጹሖች ነን እያልን እየተገዘትን ወገኖቻችንን በግፍ አለንጋ የምንገርፍ ዛሬም አለን፡፡
ምርጫችንስ ወንበዴው በርባን ነው ወይስ ጻድቁ ክርስቶስ ነው? ጦረኛውን በርባንን ነው ወይስ ሰላማዊውን ክርስቶስን ነው? የወገኖቹን ደም የሚያፈሰውን በርባንን ነው ወይስ ስለ ወገኖቹ ደሙን ያፈሰሰውን ክርስቶስን ነው? ዛሬም በዓለማችን ብዙ በርባኖች አሉ፡፡ የእኛም ምርጫ በርባኖችን ሆኗል፡፡ ረቂቁን በርባን ዲያቢሎስን መርጠናል፡፡ ክርስቶስን አስወግደው እንዳሉ ከልባችን ክርስቶስን አስወግደነዋል፡፡ ከሕይወታችን ለይተነዋል፡፡ ክርስቶስ የሞተለትን ሰውነት ከጽድቅ አራቁተን ከተገኘን ክርስቶስን ገፈፍነው ማለት ነው፡፡ የበላነው ሥጋው የጠጣነው ደሙ በውስጣችን አለና፡፡
ዛሬ የክርስቶስን የፈራጅነትና የሁሉን ቻይነት ሥልጣን ገፍፈው አማላጅ የሚሉት አሉ፡፡ የፈጣሪነቱንም ክብር ገፍፈው ፍጡርም ብለውታል፡፡ እሱ ግን ፈራጅ እንጂ አማላጅ ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለም፡፡ በተዋሕዶ የከበረ የአብ ልጅ የማርያም ልጅ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የለም፡፡ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ ለክርስቶስ የሚገባውን ክብር አለመስጠትም ልብሱን እንደ መግፈፍ ይቆጠራል፡፡
ከጭፍሮች አንዱ በስለታም ጦር ጎኑን እንደወጋው በክህደትና በጥርጥር ጦር እየወጋነው ነው፡፡ በኃጢአት የቆሸሸው በበደል የረከሰው ሕይወታችን ለክርስቶስ የጎን ውጋቱ ነው፡፡ የክፉ ምግባራቸው ተባባሪ ሆነን የጭካኔ ጦር ዛሬም በእጃችን አለ፡፡ በጦር ከተወጋ በነገር የተወጋ እንዲሉ በነገር ጦር ስንቱን አቁስለናል? የትዕቢት ጦር የመዘዝን የለንም? በእኛ ምክንያት በሐዘን ጦር ተወግተው የወደቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከክርስቶስ ጎን ደምና ውኃ እንደፈሰሰ ደም እንባ የሚያለቅሱ ክርስቶሳውያን ዛሬም አሉ፡፡
በክፉ ሥራችን የእግዚአብሔር ምሕረት ወደ መዓት፣ ትዕግሥቱ ወደ ቁጣ እንዲለወጥ በማድረግ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለምሕረት፣ ለረድኤት፣ ለበረከት፣ ለቸርነት የተዘረጋው ቅዱስ እጁ እንዲታጠፍ ካደረግን፤ እጁን የኋሊት ጠፍሮ እንደማሰር ነው፡፡ እሱ እጁን ዘርግቶ እንካችሁ ተቀበሉ ሲለን አንቀበልም ማለት እጁን የኋሊት ማሰር ነው፡፡ የዛሬው የክርስቶስ ሥቃይ ይህ ነው፡፡
አስማተኝነቱ፣ ሴሰኝነቱ፣ ነፍሰ ገዳይነቱ፣ አምልኮተ ጣዖቱ፣ ሐሰተኝነቱ፣ ይህ የዘመናችን ችንካር ነው፡፡ ትዕቢቱ፣ ስስቱ፣ ገንዘብ መውደዱ፣ ይህም ችንካር ነው፡፡ ክርስቶስ የተንገላታለት፣ ሥጋውን የቆረሰለትና ደሙን ያፈሰሰለት፣ ሕይወቱን የካሰለት ሕዝብ እንዲህ ሆኖ ሲያገኘው እጁጉን ያዝናል፡፡ እንደመስቀሉ ችንካር ያቆስለዋል፡፡
በሐዋርያት ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስን ስብከት የሰሙት ሕዝብ ‹‹እንግዲህ ምን እናድርግ?›› እንዳሉ እኛም አሁኑኑ ‹‹ምን እናድርግ?›› ልንል ይገባናል፡፡ የምናደርገውም ነገር ቀላል ነው፡፡ ንስሐ መግባት፣ ከኃጢአት መመለስ፣ ከበደል መራቅ፣ ወደ ቀራንዮ ማቅናት፣ ወደ መስቀሉ መመልከት ነው፡፡ ጌታ የሚወደው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ በመስቀሉ ፊት ቆሞ እንደተገኘ የእናት አማላጅ ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዳገኘ፣ እኛም እንደተወደዱ ልጆች ከመስቀሉ ፊት አንጥፋ፡፡ ‹‹እነኋት እናትህ›› ተብላ በዮሐንስ በኩል የተሰጠችንን የአደራ እናት ይዘን እንገኝ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታን ከእናቱ ጋር ያገኘው በቀራንዮ ነው፡፡፡ ስለዚህ እኛም ወደ ቀራንዮ እንጓዝ፡፡ ጌታን ከእናቱ ጋር እንድናገኝ፤ አባትም እናትም እንዲኖረን፣ የዛሬዋ ቀራንዮ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ዕለት ዕለት አማናዊው የክርስቶስ ሥጋ ይቆረስባታል፡፡ ደሙ ይፈስባታል፡፡ በክርስቶስ ደም የከበረው መስቀል በክብር አለ፡፡ የበደል ግድግዳ የፈረሰበት ጥል የተባለ ዲያቢሎስ የተገደለበት ነውና፡፡ ዛሬም ሰላም ያገኘንበትን መስቀል እናከብረዋለን እንሳለመዋለን፡፡ በመስቀል ምልክትም ጥንተ ጠላታችንን ዲያቢሎስን እንቀጠቅጥበታለን፡፡ ተቃጠልኩ አረርኩ እናሰኝበታለን፡፡ በሲዖል ሲያቃጥለን የነበረውን ጠላት ዛሬ ተራችንን በክርስቶስ መስቀል እናቃጥለዋለን፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በቀራንዮ ያገኛትን ዘለዓለማዊት ድንግል ቅድስት ማርያምን ከተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እናገኛታለን፡፡ የአማላጅነቷ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ ጌታ በመጨረሻው ሰዓት በመስቀል ላይ ሆኖ እንደ ኑዛዜ ቢሉ ወይም እንደ አደራ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለዮሐንስ በዘለዓለማዊ ቃሉ ‹‹እነኋት እናትህ›› እንዳለው ዛሬም መሠረቷም ጉልላቷም ክርስቶስ የሆነ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱን ክርስቲያን በዘለዓለማዊው የጌታ ቃል ‹‹እነኋት እናትህ›› ትለዋለች፡፡ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር ዮሐንስን ሆኖ መስቀሉ ሥር መገኘት ነው፡፡ ዮሐንስ የጌታን ቃል አክብሮ እናቴ ብሎ ወደ ቤቱ እንዳስገባት እኛም እናቴ ብለን ቤት ወደሚባል ልባችን ማስገባት ይኸም የክርስቶስን የኑዛዜ ቃል መጠበቅ የአደራ ቃሉን ማክበር ነው፡፡ እሱ ‹‹የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል›› እንዳለ እውነት የምንወደው ከሆነ ቃሉን እንጠብቅ (ዮሐ.14÷23)፡፡
አይሁድ ክርስቶስን እንደጠሉት እኛም አንጥላው፡፡ እውነተኛ መብል የክርስቶስ ሥጋ እውነተኛ መጠጥ የክርስቶስ ደም መጥላት በየምክንያቱም ከእርሱ መራቅ ክርስቶስን መጥላት ነው፡፡ መጨነቅ መጠበብ የእንስሳት ሥጋ እና የዓሣ ሥጋ ቀረብኝ ብሎ ሳይሆን የቀራንዮው በግ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ለምን ይቅርብኝ ብሎ ነው፡፡ አይሁድ ክርስቶስን አልተቀበሉትም፤ አራቁት (ሰቀሉት) እንጂ፡፡ እኛም ሥጋውና ደሙን አልተቀበልንም፤ አራቅነው እንጁ፡፡ ስለዚህ ወደ ሕይወት መድኃኒት እንቅረብ፡፡
በዚህ የተቀደሰው ሳምንት ይህንን የጌታን ውለታና የድኅነት ሥራ እናስተውል፡፡[/B]
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
Tuesday, March 30, 2010 9:04:15 AM
በመ/ር መንግሥተአብ አበጋዝ
በነቢዩ ኢሳይያስ «ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፤ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፣ ሕመማችንንም ተሸከመ፣ እኛ ግን እንደተመታ፣ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሰፈ፣ እንደተቸገረም ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡» /ኢሳ. 53፣4-7/ ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ፣ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ ከሆሣዕና ማግስት እስከ ትንሣኤ ያለው የጾመ እግዚእነ መዝጊያ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡
በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው፣ ከሐሜት፣ ከነገርና ከኃጢአት ርቀው፤ የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ፣ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ሲሰሙ፣ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /በዘጠኝ/ ሰዓት፣ በሰርክ /በዐሥራ አንድ/ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፣ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፣ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራ ሥቃይን እና 5ሺ 5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም የምናስታውስበት ሳም ንት ነው፡፡ በዕለት በዕለት ከፍለን በየትኛው ቀን ምን ተደረገ እያልን እንጠይቅ?
ሰኞ፡-
ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ በምትባል መንደር ያድራል በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ /ማር. 11፣11-14/ ቅጠል ያላትን በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፣ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ዕለት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፡፡
ትርጓሜ፤ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች፣ ሃይማኖትና ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤልን ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡
በለስ ኦሪት ናት፡- ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡
በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች... እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ.21፣13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም ይባላል፡፡
ማክሰኞ፡-
ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተመቅደስ ምክንያት፣ ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን፣ ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፤ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡
ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን፣ በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? የሚል ነበር፡፡ /ማቴ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣7-35፣ ሉቃ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣27-33፣ ሉቃ. 20፣1-8/፤ እርሱም ሲመልስ፤ «እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፣ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን እዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረ፣ ከሰማይን? ወይስ ከሰዉ? በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ወይስ በሰው ፈቃድ?» አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል፤ ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፣ እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን፤ ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው» ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተዉት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ እንጂ፡፡
በማቴ. 21፣28፣ ምዕ. 25፣46፣ ማር. 12፣2፣ ምዕ. 13፣37፣ ሉቃ. 20፣9፣ ምዕ. 21፣38 የሚገኙት ትምህርቶች ሁሉም የማክሰኞ ትምህርት ይባላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ፣ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡
ረቡዕ፡-
ምክረ አይሁድ ይባላል፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ፣ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ. 26፣1-14፣ ማር. 14፣1-2፣ ቁ 10፣11፣ ሉቃ. 22፣1-6/፤ የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚሁ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ሐዋርያት ከጌታችን መያዝ በኋላ በኀዘን በፍርሐት እንደነበሩ እያሰቡ መጻሕፍትን በማንበብ በጾም፣ በጸሎ ትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡
የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ፣ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት፣ /ባለሽቱዋ ማርያም/፤ «ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ፣ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ» ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ፣ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ነው፡፡ ረቡዕ የመዓዛ ቀን የተባለው፡፡
ረቡዕ የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ፣ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፤ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ /ማቴ. 26፣6-13፣ ማር. 14፣.9፣ ዮሐ. 12፣8/ ኃጢአትን በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ከምታስተምረን ማርያም እንተ እፍረት እንባን ለንስሐ ሕይወት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ሐሙስ፡-
በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡
ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ /ማቴ. 26፣36-46 ዮሐ. 17/፡፡
ሕፅበተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡
የምስጢር ቀን ይባላል፡፡ ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡
የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል /ሉቃ. 22፣20/ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ተባለ፡፡
የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡ ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት /ዮሐ. 15፣15/፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባል በትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡
የጸሎተ ሐሙስ ምስጢራት በብሉይ ኪዳን
ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል፡፡ ዝግጅቱም በሦስቱ ወንጌላት ላይ ተመዝግቧል /ማቴ. 26.7-13/፡፡ ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን በግብፅ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡ ሙሴም ለሕዝቡ ነገረ፣ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፡፡ መቅሰፍት ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብፃውያንን ቤት በሞተ በኲር ሲመታ፣ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው፡፡ /ዘጸ. 12፣1-20/፡፡ በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በ14ኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኲር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናልና፡፡ «ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው» /1ቆሮ. 5፣7 1ጴጥ. 1፣18-19/
በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ሁሉ በዮሐ. 14፣16 የሚገኘውን ለደቀመዛሙርቱ ረጅም ትምህርት አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምስጢረ ሥላሴ የሦስትነት ትምህርት፣ ምስጢረ ሥጋዌ /የአምላክ ሰው መሆን/፣ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን /የዳግም ምጽአቱን ነገር/ ነው፡፡ እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም እሱ እያስተማራቸው ሳለ ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድ ተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቆ መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ቀን ነው፡፡ ማቴ. 26፣47-58
ዓርብ-
የስቅለት ዓርብ ይባላል፡፡ የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ መዋሉን ለማስታወስ ነው፡፡ /ማቴ. 27፣35/፡፡
መልካሙ ዓርብ ይባላል፡፡ ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት አንድ ሰው ሲያጠፋ ተሰቅሎ ይሞታል፡፡ በሮማውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስለ አደረገው፣ በሞቱ መልካሙን ሕይወትን ስለአገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡
የትንሣኤን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ ምእመናን ሁሉ በዕለተ ዓርብ መከራውን ለማሰብ ከቤተ ጲላጦስ እስከ ጎልጎታ መቃብረ ክርስቶስ ድረስ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ጉዞ የሚደረግባቸውም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የተፈጸሙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው መከራውን በማሰብ ሲሰግዱ የሚውሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ በስም ክርስቲያን ተብለን ከምንጠራው መካከል፣ ተድላ ደስታ በሚፈጸምባ ቸው ሥፍራዎች ክፉ ሥራ ስንፈጽም የምንውል አንጠፋም፡፡ እንዲህ የምናደርግ ሁሉ በአለፈው ልንጸጸትና በቀሪ ዘመናችን ልንታረም ይገባል፡፡ በዓመት አንዴ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን የምናስብበት፤ ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለ ምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን ኃጢአት ስንሠራ የምንውልበት ሊሆን አይገባም፡፡
ቅዳሜ-
ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምት ውል የተሻረችው ቅዳሜ ተብላለች፡፡
ለምለም ቅዳሜ ካህናቱ ለምእመ ናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሠይሟል፡፡ ቀጤ ማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡
ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፤ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷ ታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘ ለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡ የዕለታ ቱን ክብርና ሥያሜ ከማወቅና ከመ ረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡[/B]
ምንጭ- መጽሐፈ ግብረ ሕማማት
-ሐመርና መለከት መጽሔቶች
ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም
1 2 3 4 Next »