Skip navigation.

Chiesa Ortodossa Etiopica Tewahedo(Unitaria)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኢጣሊያ ሚላኖ

ተአምርህን አየን


የምስጋና ቅኔ በፊትህ ለማቅረብ፣
ማለፍ ነበረብን አስፈሪውን ወጀብ፣
አንተ ብትረዳን አንተ ብታግዘን፣
ታይተው ነበር ጠፉ ከመባል አዳንከን።
የትኛው ግብራችን ከሞት አተረፈን ፣
ቸርነትህ እንጂ በሕይወት ያቆየን።
መንገድ ስተን ወጥተን ተጋልጠን ለአደጋ፣
ማዕበል ወጀብ ገጥሞን እጅግ የሚያሰጋ፣
ድንግል ከለለችን ግርማ ሞገስ ሆና፣
ስሟን ጠርተን አንዴም አላፈርንምና።
በመከራው ሰዓት በዚያ ጭንቅ ቦታ፣
ስምሽን ጠራን ድንግል ስምህን ተራን ጌታ።
ጩኸት ሲበረክት ደጃፉ ተዘግቶ፣
ለጸሎት በረታን አፋችን ተከፍቶ።
አይዟችሁ ለማለት ወገን ሳይመጣልን፣
ባእዳን ደርሰው ነው የተንከባከቡን።
አባት በዚያች ሰዓት እንዲያ ስንሸበር፣
እጅ እግር እያለን ከብዶን መዘዋወር፣
የላካቸው ሰዎች ፈጥነው ደረሱልን፣
ዝማሬው ሲጀመር በሩን ከፈቱልን።
የደረሱት ሰዎች ተጨንቀው በብርቱ፣
አስክሬን ፍለጋ ደጃፉን ሲከፍቱ፣
አፋችን ሲናገር ስንራመድ አይተው፣
እጅግ ተደነቁ ማመን ተሳናቸው።
በሰው ግምት ሞትን <አይተርፉም> ተብለን፣
አንተ ግን ጠብቀህ ለምስጋና አቆምከን።
በአውድ ምሕረት ቆመው ስምህን የጠሩ፣
<ወሮታህ ብዙ ነው> ብለው የዘመሩ፣
የማዳንህን ነገር ጥበቃህን አይተው፣
የደስታ ለቅሶ አነቡ ተቃቅፈው።
የመጣው አደጋ ድንገት የደረሰው፣
ሥልጣን አልባ ነበር በጁ ሞት የለሌለው።
መስኮት ገነጠለ መስተዋት ሰበረ፣
የነበረው ሥልጣን ይህ ብቻ ነበረ።
ነፍሳችንን አዳንክ መጡ መላእክትህ፣
ከአደጋ ከለሉን ዳኑ አገልጋዮችህ።
ፈጣን ተሽከርካሪ እንዲያ እየበረረ፣
ኃይሉን ቀጥ አድርገህ ውሃ ይዞት ቀረ።
ተዓምርህ ጀመረ ዛሬም እንደ ትናንት፣
ለኛ ስብከት ሆነ የማዳንህ ብሥራት።
ከባዱን አደጋ በእለተ እስጢፋኖስ፣
ቀላል አደረግኸው ድል ነሳን ክርስቶስ።
የጨበጥነው መሪ መች አስተማመነን፣
አንተ ፈጥነህ ደረስክ ምድሪቱ ስትክደን
ድንቅ አደረግህልን ተዓምርህን አየን፣
በሣቅ ተቀየረ የነበረን ኅዘን።

በምድረ በዳው ላይ ክብርህ ተገለጠ፣
ከሞት አተረፍከን ታሪክ ተለወጠ።
ለቅሷችንን በሳቅ ኅዘኑን በደስታ፣
የእስራኤል ቅዱስ ለወጥክልን ጌታ።
<አለቀ አበቃለት ተቆረጠ> ሲባል፣
እጅህ ካረፈበት ዳግም ይቀጠላል።
ቸር አባት ነህና እንዲህ ነፍስ ይዘራል፣
እንኳን የወደቀው የሞተው ይነሣል።
ሰምተን ነበር አየን ድንቅ ታደርጋለህ፣
እግዚአብሔር በወጀብ በአውሎ መንድ አለህ
ከቁጥር ሳንጎል እንደወጣን ሳንቀር፣
ልንመሰክር ቆምን የክብርህን ነገር።
ታይተው ነበር ጠፋ መባሉ ቀረና፣
እግዚአብሔር በፊትህ ቆምን ለምስጋና።
ታላቅ መልእክት አለ ያስተላለፍክልን፣
ምሥጢር ገላጭ አምላክ ምሥጢር ግለጽልን
ይህ ነው ልመናችን አምላካችን ስማን፣
ከሕይወት ገበታ ከቤትህ አታውጣን።
ሳንዘጋጅ አይሁን ያ የመምጫህ ሰዓት፣
አብቃን ለንስሃ እግዚአብሔር የኛ አባት።
የማይቀር እንግዳ ስሙ <ሞት> የሚባል፣
ባልታሰበ ሰዓት በድንገት ይመጣል።
ጥሪ ደርሶን ነበር ቀን ሲመሽ በማታ፣
አዳነን ክርስቶስ የድንግል ልጅ ጌታ።
ከደም መፍሰስ ዳንን ከአጥንት ስብራት፣
ከኛ ጋራ ብትሆኝ የአማኑኤል እናት።
የእናትነት ፍቅርሽ ድንግል ሆይ ደረሰን፣
ምልጃ ቃል ኪዳንሽ ከሞት አተረፈን።
ቤትሽን ለመርገጥ እድል ያድረሰን፣
ፈተናው በዝቶብን ከመንገድ የቀረን፣
ዳግም እንመጣለን ቤትሽ ለመሰብሰብ፣
ስምሽን እየጠራን ምስጋና ለማቅረብ።
ቃል ገብተናል ዛሬ ቃል ጠባቂ ያርገን፣
ምስጋና ለማቅረብ ከበሮውን ይዘን።
የበረቱት ልጆች ወጀቡን ሳይፈሩ፣
ለምስጋና ደርሰው በቤትሽ ዘመሩ።
ታላቅ ምስጋና ነው ዛሬ የምናቀርበው፣
በእግዚአብሔ ጥበቃ ከሞት የተረፍነው።
ቤተ እግዚአብሔር ቆመው ላሰቡን አባቶች፣
ለተጨነቁልን ላነቡት እናቶች።
መሥዋዕት ለከፈሉት ወንድሞች እህቶች፣
አዝነው ላለቀሱት ለክርስቶስ ልጆች።
ሁሉንበአንተ አለፍነው ሁሉን አንተ አርገኻል
ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይገባኻል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አብርሃም ሰሎሞን የካቲት 25/1999


ሥራ ሕይወት ነው" እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ ስለ በደላችንም ደቀቀ " ኢሳ 53፥5

Write a comment

You must be logged in to write a comment. If you're not a registered member, please sign up.

December 2009
S M T W T F S
November 2009January 2010
1 2 3 4 5
6 7 8 9 10 11 12
13 14 15 16 17 18 19
20 21 22 23 24 25 26
27 28 29 30 31