“እግዚአብሔር በአንድም መንገድ በሌላም ይናገራል፡፡” ኢዮ. 33 ፡14 ፡፡
Friday, 23. March 2007, 20:41:59
“እግዚአብሔር በአንድም መንገድ በሌላም ይናገራል፡፡” ኢዮ. 33 ፡14 ፡፡
ክርስትና ጥላቻን አይሸከምም
ክርስትና የተመሠረተው በፍቅር ላይ ነው፡፡ ያውም ሊተረጎም በማይችል ፍቅር ላይ ፡፡ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሠረተው ልዩ ፍቅር ላይ፡፡ የክርስትና መመሪያው “ጠላትህን ውደድ” ነው፡፡ ለዚያውም ክርስቲያን ከዲያብሎስ በቀር ጠላት የለውም፡፡ ግን አንተ ባትጣላውም እርሱ የሚጠላህን፣ አንተ ክፉ ባታደርግበትም እርሱ ክፉ የሚያደርግብህን ውደድ ሲል ነው፡፡
በክርስቲያኖች መካከል ልዩነቶች ባይኖሩ ይመረጣል፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው መኖር ቢችሉ ጠላታቸው ዲያብሎስ ያፍራል፣አባታቸው እግዚአብሔር ይደሰታል፡፡ እነርሱም መለያየት ከሚያስከትለው ፈተና ይድናሉ፡፡ ይሁን እንጂ በክርስቲያኖች መካከል መሠረታዊ ያልሆኑና የሆኑ ልዩነቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ መሠረታዊ ልዩነቶች የምንላቸው በሃይማኖት የተነሳ የሚከሰቱ ልዩነቶችን ነው፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ዲያብሎስ በሰዎች እያደረ በሚዘረው እንክርዳድ ምክንያት ሚከሰቱ ናቸው፡፡ አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት ከሚለው የሐዋርያው ትምህርት የሚወጣ /ኤፌ 4 ፡ 5/፡ እውነትን በመቀበልና ባለመቀበል መካከል የሚደረግ ተጋድሎን የሚያስከትል በመሆኑ ከጥንት ጀምሮ የዚህ ልዩነት ምንጩም፣ አመንጭዎችም ሲወገዙ ኖረዋል፡ ይኖራሉም፡፡
ይህም ቢሆን የተለየው ወገን እንዲመለስ፣ እንዲያምን ይደረጋል፣ ካላመነ ካልተመለሰም ተወግዞ ይለያል እንጂ ይውደም ፣ይሙት፣ ይጥፋ ተብሎ ምድራዊ ቅጣት አይታዘዝበትም፡፡የጠላትነት ስሜት ተፈጥሮ /እንዲፈጠር ሆኖ/ ዓይንህን አልየው ድምፅህን አልስማው አይባልም፡፡ እንኳን በሃይማኖት የሚመለሱ ወገኖቹን ይቅርና ሌሎቹንም የሰው ዘሮች ቢሆን ፍቅር ከማሳየት ውጪ የማጥፋትና የማስወገድ መርህ ለክርስቲያን ሊኖረው አይገባም፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከሙስሊም ወገኖቻቸው ጋር በተዐቅቦ ተከባብረውና ተፋቅረው የኖሩት በዚህ መሠረታዊ ትምህርት የተነሣ ነው፡፡ የገዛ ወገኖቻቸው ያሳደዷቸውን የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ቦታ ሰጥተው፣ሕይወታቸውን ታድገው፣ለጠላቶቻቸው አሳልፈው ሳይሰጡ የተንከባከቧቸው በዚህ የተነሣ ነበር፡፡
በክርስቲያኖች መካከል መሠረታዊ ያልሆነ ልዩነት ሊኖርም ይችላል፡፡ በዘር፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካዊ አመለካከት፣ በሥልጣን ክፍፍል፣ በሀብት ክፍፍል፣ በዜግነት፣ በመልክና በቁመና፣በዕውቀት፣ ወዘተ… መለያየቶች ቢኖሩም እንኳን ክርስቲያናዊ እምነትና ሕይወት አቻችሎ፣ አስማምቶና አዋህዶ ያለበለዚያም ልዩነቶቹን ኅብረ ውበት አድርጎ ቆጥሮ ይጓዛል እንጂ መሠረታዊውን የፍቅር ኑሮ አናግተው ለጥላቻና ለመለያት አያደርጉም፡፡ ክርስትና የተማረውን /ምሁር የሆነውን/ ጳውሎስ ከዓሣ አጥማጅ ጴጥሮስጋር፣ ቀራጩ ማቴዎስን ከሰዓሊው ሉቃስ ጋር፣ ንጉሡ ካሌብን፣ ከገበሬው ዜና ማርቆስ ጋር፣ሮማዊውን ዲዮናስዮስ ከዕብራዊው ቶማስ ጋር፣ግባጻዊውን አትናቴዎስ ከሶርያዊው ከኤፍሬም ጋር፣ ያስተሳሰረች ሠንሠለት ናት፡፡ የዘር ልዩነቶች የክርስትና ኑሮ ውስጥ ከልዩነት አይቆጠሩም፡፡ ስንዴ ለመገበሪያ የሚውለው የት ተዘርቶ በቀለ በሚል ሳይሆን ስንዴው ራሱ ንጹሕ ነው ወይ? በሚለው መመዘኛ ነውና፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ የሚከበሩትን ያህል በግብጽ ይከበራሉ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተወለደበት ከልዳ በበለጠ በኢትዮጵያ ይከበራል፣ፍሬምናጦስን በሀገሩ በግሪክ የሚያስታውሰው ባይኖርም ኢትዮጵያውያን ግን ከሣቴ ብርሃን እያሉ ያከብሩታል፡፡
ሰዱቃውያን ፈሪሳውያን ጳውሎስ የአመለካከት ልዩነታቸው ወደ ክርስትና እንዳይመጡ አላደረጋቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እርስ በርስ ከማይዋደዱት ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት እና ከሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት መካከል ቅዱሳንን ሰይማ ታከብራለች፡፡ ቅዱስ ላሊበላን ቅዱስ ቴዎድሮስን /ወልደ ንጉሥ ዳዊት/ መጥቀሱ ይበቃል፡፡
ፖለቲካዊ አመለካከቶች የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች እንጂ ክርስቲያናዊ ልዩነቶች እና የጥላቻ መንሥኤዎች ተደርገው መወሰድ የለባቸውም፡፡ሶሻሊስቱም፣ ሶሻል ዲሞክራቱም፣ ሪፖብሊካኑም፣ አብዮታዊ ዲሞክራቱም፣ ሌላውም ሌላውም ያላቸውን የአመለካከት ልዩነት ልዩነት አቻችለው በአንዲት ቤተ ክርስቲያን መኖር፣ ማስቀደስ መቁረብ ይችላሉ፡፡ ልዩነታቸው መሠረታዊ አይደለምና ዘርን፣ አመለካከትን፣ ሥልጣንን ወዘተ… መሠረት አድርገው የሚነሱ የጥላቻ ስሜቶችን ለማስተናገድ ክርስተና ቦታ የለውም፡፡ ከባሕሪው ጋርም አይሄድም፡፡ ከቁ ስጥንጥንያ ቤተ መንግሥት የወጣው አርሳንዮስ ከግብጽ ከመጣው መቃርስ ጋር በአንድ ገዳም ኖሯል፡፡ ፍቅር ስላሸነፈ፡፡ ክርስትና እነዚህን ልዩነቶች ድል ነሥቶ የበላይ ካልሆነ የንን ህይወት ክርስትና ነው ማለት ያዳግታል፡፡ አንዱ መለያው ይህ ነውና፡፡ ይህ ወንድሜ አመለካከቱ እንዲሁ ነው፡ እኔ አልቀበለውም ከማለት ባለፈ በዚህ አመለካከቱ የተነሣ አልወደውም፣ እርቀዋለሁ፣ ይጥፋ፣ይሙት በቃ፣ ይወገድ፣ ይውደም የሚለው ዛቻ የተሞላበት አካሄድ ፈጽሞ ክርስቲያናዊ አይሆንም፡፡ ይኸኛው ዘር ይጥፋ፣ ይኸኛው ዘር ይወገድ፣ያኛውን ዘር አትቅረቡ፣ ሌላውን ወገን ውደዱ የሚለው መሥመር ሰይጣናዊ እንጂ ክርስቶሳዊ አይደለም እርሱማ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ነው ያለው፡፡
በመሆኑም ከክርስቲያናዊ የፍቅር ሕይወት ጋር የሚቃረነው የጥላቻ ስሜት በልቦናችን ድሩን እንዳያደራ፣ ፍሬዎቹን መለያትንና መገዳደልንም /መጠፋፋትን/ በመንፈሳዊው የፍቅርና የመቻቻል ሽቱ እናጥፋው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

